በኢትዮጵያ ክብርና ብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚመጣን ማንኛውንም እንቅስቃሴ እንደማይታገስ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስገነዘበ።

204

በኢትዮጵያ ክብርና ብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚመጣን ማንኛውንም እንቅስቃሴ እንደማይታገስ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስገነዘበ።

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ የሀገርን ጥቅም በሚጻረር መልኩ ሲንቀሳቀሱ ያገኛቸውን ሦስት ግብረ-ሰናይ ድርጅት ላይ እገዳ ጥሏል።

አንድ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የሀገሪቷን ሕግና ደንብ አክብሮ የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚያቃልሉ ሥራዎች ላይ በስፋት ይሳተፋል።

ግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ የሚጠበቅባቸውን እያከናወኑ አለመሆኑን መንግሥት በተደጋጋሚ ማስታወቁ ይታወሳል።

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ ቀደም ብሎ ይሄንኑ በተመለከተ በሰጠው መግለጫ፤ ስደተኞችን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት አጋር አካላት የተፈለገውን ያህል እንደማይንቀሳቀሱ ማስታወቁ አይዘነጋም።

አጋር አካላቱ በሚፈለገው መጠን ሥራቸውን እየሰሩ አለመሆናቸውንም ነው ያስታወቀው።

ተቋማቱ በገቡት የውል ስምምነት መሰረት የሚያሥፈልገውን ሁሉ እንዲያቀርቡም በማሳሰብ፤ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ግን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ጠቁሞ ነበር።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ለድርጅቶቹ የሥራ ፍቃድ ይሰጣል፤ ሥራቸውንም በአግባቡ እየሰሩ መሆኑን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል።

ይህንንም ተከትሎ ኤጀንሲ ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ የአገርን ጥቅም በሚጻረር መልኩ ሲንቀሳቀሱ ያገኛቸውን ሦስት ግብረ-ሰናይ ድርጅቶችን አግዷል።

ድርጅቶቹም ኤም ኤስ ኤፍ ሆላንድ፣ ኖርዊጂያን ሪፊዩጅ ካውንስልና ማክቶም ፋውንዴሽን ናቸው።

የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ማንኛውም ግብረ ሰናይ ድርጅት ኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ሊያከብር ይገባል።

ያም ሆኖ ሦስቱ ድርጅቶች ከዚህ በተቃራኒ አዋጁንም ሆነ የአገሪቷን ሉዓላዊነት በሚጥስ መልኩ ሲንቀሳቀሱ መገኘታቸውን ነው ያረጋገጡት።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“የትህነግ አሸባሪ ቡድን ካልጠፋ በስተቀር በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ሊኖር እንደማይችል አሜሪካ ልትገነዘብ ይገባል” የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት
Next articleየአሜሪካው ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) ኃላፊ ሳማንታ ፓወር አሸባሪው ሕወሃት እያደረገ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳሳሰባቸው ገለጹ።