“እነሱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል ለመጓዝ ወደዋል፤ እኛ ደግሞ ኢትዮጵያን ለመታደግ እነሱን እስከ ሲኦል ደጃፍ ድረስ ከመሸኘት አንዝልም” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

322

“እነሱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲኦል ለመጓዝ ወደዋል፤ እኛ ደግሞ ኢትዮጵያን ለመታደግ እነሱን እስከ ሲኦል ደጃፍ ድረስ ከመሸኘት አንዝልም” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳይ እንደተናገሩት አሸባሪው የትህነግ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያነገበውን የጥፋት ራዕይ ለማሳካት እንዲቻለው ቅድሚያ የአማራን ዘር በማጥፋት ተግባር ላይ ከተሰማራ ከ50 ዓመታት በላይ አልፎታል፡፡ ከ1970ዎቹ እስከ አሁንም ድረስም አልታቀበም፤ ለዚህ እውነታ የወልቃይት እና የማይካድራ ምድር ህያው እማኞች ናቸው ብለዋል፡፡

ስለ ሰው ልጆች የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ተቆርቋሪ ነን የሚሉት አንዳንድ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የትህነግን እኩይ ሥራ ከማውገዝ ይልቅ ከወልቃይት እስከ ማይካድራ ምድር ድረስ በድብቅና በገሃድ በፈጸማቸው የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ሁሉ አይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ መሆንን መርጠዋል ነው ያሉት፡፡

አቶ ግዛቸው እንዳሉት በግብረ ሠናይ ድርጅት ስም ቢቋቋሙም ህብረታቸው ግን ከግብረ እኩይ ቡድኖች ጋር መሆኑን ዛሬም በሚያሳዩት ተግባር እያረጋገጡልን ይገኛሉ፡፡ አሸባሪው ትህነግ የአማራን ዘር ለማጥፋት በተጓዘው የ50 ዓመታት የጥፋት ጉዞው ሁሉ እነዚህ አካላት በእርዳታ ሥም ከሚያስገቡት የስንዴ ቋጠሮ ጋር ነፍጥ እየቋጠሩ ከበርሃ እስከ ቤተ መንግሥት ሲጋልቡት ኖረዋል፤ ዛሬም የትህነግ ጠበቃ ሆነው ነጻነታችንን በስንዴ እንድንለውጥ ለባርነት አጭተውናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊነታችንን በምጽዋት ከሚሠጡት ስንዴ ያነሰ መሆንን ለማሳመን ነጋ ጠባ ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያልወረወሩብን አለት የለም ያሉት አቶ ግዛቸው በሰብዓዊ እርዳታ ስም ፖለቲካዊ ቀንበራቸውን ለመጫን የዛቻ ናዳ እያወረዱ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

“ረስተውት እንጂ ኢትዮጵያውያን ነጻነታቸውን ለመግፈፍ የተቃጣባቸውን ዲፕሎማሲ ቀመስ ዛቻ እንደምን ባለ መንገድ እንደመከቱት እቴጌ ጣይቱን ታሪክ ለአፍታ ያህል ማስታወስ ይበቃል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ነጻነታችንን በስንዴ፤ ብኩርናችንን በምስር የምንለውጥ ከንቱዎች አይደለንም” ብለዋል፡፡

በትናንሽ ድሎች የምንኩራራ፣ በጥቃቅን ስህተቶች የምንበረግግ ድንጉጥ ሕዝቦች አይደለንም፤ ባንዳነትን ከወራሪነት አሳንሰን አናይም፤ ለሁለቱም ምህረት አልነበረንም፤ ዛሬም የለንም ነው ያሉት፡፡

“አባቶቻችን በትላንቶቹ ወራሪዎችና በተላላኪ ባንዳዎቻቸው ላይ ያሳረፏቸው ሰይፎች ምስክር ናቸው። የእኛ የልጆቻቸው መንገድም ይሄው ነው” ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አሸባሪው ትህነግ ከእርዳታ ስንዴ ጋር ቀብድ የተቀበለውን ሀገር የማፍረስ አጀንዳ ለመፈጸም እስከ ሲዖል ድረስ ለመግባት ወስኖ ጉዞ መጀመሩን ገልጸው ኢትዮጵያን ለመታደግ እኛደግሞ እነሱን እስከ ሲኦል ደጃፍ ድረስ ከመሸኘት አልዛልንም ነው ያሉት፡፡ አሁንም እየፈጸምን የምንገኘው ራስን የመከላከል ተጋድሎ ለአሸባሪው ትህነግ ከሚደረግለት መመለሻ የሌለው ሲኦላዊ ሽኝት ማዕቀፎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ የሲኦል ሽኝት ተጋድሎ ላይ ተቀናጅተው የተሰለፉት የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ እንዲሁም የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ኃይሎች ትህነግን ወደ ሲኦል ከመሸኘት የሚዝል ክንድም ሆነ የሚያዝን ልብ እንደሌለም አስገንዝበዋል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“ከወገን ጦር ጋር ጠላትን በመፋለም ህልውናችንን እናረጋግጣለን” የአዲአርቃይ ወረዳ ሚሊሻዎች
Next articleአሸባሪው ሕወሓት በታዳጊዎች ላይ የጦር ወንጀል እየፈጸመ መሆኑ ተገለጸ።