
“ታሪክ ለማስተማር ሳይኾን ታሪክ ለመሥራት ወደ ግንባር እዘምታለሁ” በታሪክ ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዲግሪ ምሩቅ መምህር ድምበሩ አለኸኝ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር በጠላት ስትወረር እምዬ ምኒልክ የክተት አዋጅ ጥሪ ማስተላለፋቸው ይታወሳል። የአማራ ክልል መንግሥትም አሸባሪው ትህነግ በአማራ ብሎም በኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚያደርሰውን ዘረፋ፣ወረራና አስገድዶ መድፈርን ለመከላከል ሐምሌ 18/2013 ዓ.ም የክተት ጥሪ አስተላልፏል። ጥሪውን የተቀበሉ ወጣቶችም ስልጠና በመውሰድ አሸባሪውን ለመደምሰስ በሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛሉ።
ወጣት ቢራራ መልኬ የዳባት ከተማ ነዋሪ ናት። በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን እሾህ ነቅላ ለመጣል ወታደራዊ ስልጠናን በመውሰድ ለውጊያ ዝግጁ መኾኗን ተናግራለች። በወታደራዊ ስልጠናው የአካልና የሥነ ልቦና ግንባታ ማግኘቷን የገለጸችው ወጣት ቢራራ በወረዳው የሚገኙ ሴቶች አቅም ያላቸው ወደ ግንባር በመሄድ ጠላትን ይፋለማሉ፤ ወደ ግንባር የማይሄዱት ደግሞ የኋላ ደጀን በመኾን በስንቅ ዝግጅት ያግዛሉ ብላለች።
ወጣቷ ከሌሎች እህቶችና ወንድሞች ጋር በመኾን አሸባሪውን ቡድን በቆፈረው ጉድጓድ ለመቅበር መዘጋጀቷንም ተናግራለች። አሸባሪው ትህነግ ለሕጻናት አደንዛዥ ዕጽ እየሰጠ ያለዕድሚያቸው የጦር መሣሪያ በማስታጠቅ ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት እየሠራ ነው ብላለች።
ሌላው የዳባት ከተማ ነዋሪ አቶ ጴጥሮስ አንዳርጌ እንደገለጹት እሳቸውና የከተማው ነዋሪዎች አሽባሪውን ትህነግ ለመደምሰስ ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ ነው። ለዚህም በቂ ስልጠና ወስደዋል። በወረዳው የሚገኝ ወጣትም የክልሉ መንግሥት ያወረደውን የክተት ጥሪ በነቂስ ተቀብሎ ዝግጅት መጨረሱን አስረድተዋል።
ሌላው የዳባት ወረዳ ነዋሪ መምህር ድምበሩ አለኸኝ በታሪክ የትምህርት ክፍል ሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል። ለህልውና ዘመቻ ያላቸውን ቁርጠኝነትም ሲገልጹ “በታሪክ ትምህርት የሁለተኛ ዲግሪ ምሩቅ ነኝ፤ አሁን ታሪክ ለማስተማር ሳይኾን ታሪክ ለመሥራት ወደ ግንባር እዘምታለሁ” ብለዋል። በህልውና ዘመቻውም ያለምንም ግፊትና ጎትጓች በራሳቸው ፈቃድ ስልጠና ወስደው እንደተዘጋጁም ነው የገለጹት።
አሸባሪዎቹ የትህነግ አባላት የባንዳነት ሥራ በኢትዮጵያ ላይ ሊደግም አይገባም ያሉት መምህር ድምበሩ “እኛም የአርበኞች ልጆች ነን፤ የአባቶችን ታሪክ በመድገም ጁንታውን አፈር እናለብሳለን” ብለዋል። የዳባት ሕዝብ ይህንን ለማድረግ አይቸገርም፤ በዳባት የሚገኘው ወጣትም የለውጥ አቀጣጣይ ነው፤ የጁንታውን ድብቅ ሴራ ለመበጣጠስ ሕዝቡ በአንድነት ተነስቷል፡፡ ውጊያውንም ከወገን ጦር ጋር በመኾን በአጭር ጊዜና በአጭር ቀን ድል እናደርጋለን ብለዋል።
ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
