የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሕዳሴ ግድብ 103 ቢሊዮን ብር ወጭ ማድረጉን አስታወቀ።

194

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሕዳሴ ግድብ 103 ቢሊዮን ብር ወጭ ማድረጉን አስታወቀ።

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ግድቡ የኔ ነው (It is my Dam) የተሰኘ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበትን መተግበሪያ ይፋ አድርጓል።

ባንኩ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን 103 ቢሊየን ብር ወጭ ማድረጉን መተግበሪያውን ይፋ ባደረገበት መርኃግብር ላይ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ እንዳሉት መተግበሪያው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከዚህ በፊት ለግድቡ ድጋፍ ሲያደርጉ ወደ ባንክ በመሄድ የሚወስድባቸውን ጊዜ የሚቆጥብ ነው፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከ20 ዶላር እስከ 10 ሽህ ዶላር ለሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት በሚገኙበት ቦታ ሆነው አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት መተግበሪያ ነው ብለዋል። ይህ ፕሮጀክት የሀገር ሃብት መሰብሰቢያ በመኾኑ እና የውጭ ምንዛሬም ስለሚያስፈልግ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ነው የጠየቁት፡፡

ሕዝቡ አሁንም ለሕዳሴ ግድብ የሚያደርገውን ድጋፍ በገንዘብም በሞራልም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትየጵያ ዲያስፖራ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ዲያስፖራው ለሀገሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ የአንድነታችን ምሰሶ የፍትሐዊ ጥያቄያችን መሰረት ለሆነው ፕሮጀክት ንግድ ባንክ ያደረገው አስተዋጽኦ ምሳሌ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባዋል ነው ያሉት። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለግድቡ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከፍተኛ ወጭ የሸፈነው ንግድ ባንክ መሆኑን በመጥቀስ አመስግነዋል። ሕዝቡ አሁንም ለፕሮጀክቱ ስኬት በገንዘብም በሞራልም እንዲደግፍ ነው የጠየቁት፡፡

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን-ከአዲስ አበባ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous article“ፖለቲኮ ዩሮፕ”ያወጣው ጽሑፍ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ እንደማይገለጽ በብራሰልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡
Next article“ታሪክ ለማስተማር ሳይኾን ታሪክ ለመሥራት ወደ ግንባር እዘምታለሁ” በታሪክ ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዲግሪ ምሩቅ መምህር ድምበሩ አለኸኝ