“ፖለቲኮ ዩሮፕ”ያወጣው ጽሑፍ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ እንደማይገለጽ በብራሰልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡

274

“ፖለቲኮ ዩሮፕ”ያወጣው ጽሑፍ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ እንደማይገለጽ በብራሰልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኤምባሲው ባሮነስ አርሚንካ ሄሊች የተባለች ጸሐፊ እ.አ.አ ነሐሴ 2/2021 “ፖለቲኮ ዩሮፕ” በተባለ እትም ላይ ስለኢትዮጵያ የጻፈችው ጽሑፍ ላይ የተሳሳተና በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሃቅ ያላገናዘበ ነው ሲል በደብዳቤ የገለጸው፡፡

ኤምባሲው በ’ፖለቲኮ ዩሮፕ’ የወጣውን ጽሑፍ አጥብቆ የኮነነ ሲሆን ይህም በተሳሳተ መረጃ ተመስርቶ የተጻፈ መሆኑን ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ለዘመናት በባህል፣ በሃይማኖት፣ በመቻቻልና በጋራ በመኖር የታወቁ ናቸው፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከልም ጠላትነት የለም፤ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ከዩጎዝላቪያ ጋር በማነጻጻር በፖለቲኮ ዩሮፕ እትም ላይ የወጣው ጽሑፍ ያልተገባ ንጽጽርና አቋም መሆኑን ኤምባሲው አመላክቷል፡፡

የመጽሔቱ ጸሐፊ ባሮንስ አርሚንካ ሄሊች ኢትዮጵያን ከዩጎዝላቪያ ጋር ለማነጻጸር መሞከሯ የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊና ባሕላዊ ኑባሬን በውል ካለመረዳት የመነጨ መሆኑን ደብዳቤው አትቷል፡፡

ኢትዮጵያን ከዩጎዝላቪያ ጋር በማኅበረ ፖለቲካ፣ በታሪክና በባህል ማነጻጻር ያልተገባ አረዳድ እንደሆነም ገልጿል፡፡

ጸሐፊዋ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባስልጣናት በትግራይ ክልል ዙሪያ ስላደረጉት ንግግርና አሸባሪው ትህነግ የተፈረጀበትን አግባብ ባለመረዳት መጻፏንም ኤምባሲው ጠቁሟል፡፡ የመንግሥት ባስልጣናት ለትግራይ ሕዝብ በጎ አመለካከት እንደሌላቸው አድርጋ ማቅረቧ የተሳሳተ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የተሳሳተና ገለልተኛ ያልሆነ መረጃን በማሰራጨት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት እንዲኖር ሆን ብላ ያደረገችው ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ግን ከጻፈችው በተቃራኒ መሆኑን አንስቷል፡፡

ሽብርተኛው ትህነግ በሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊትና በዜጎች ላይ በፈጸመው የሽብር ጥቃት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ እንደተፈረጀ ኤምባሲው በጻፈው ደብዳቤ አመላክቷል፡፡ ኤምባሲው የአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት እንደፈጸመ አስታውሷል፡፡

በሀገሪቱ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ያደረጉ የአሸባሪ ቡድኑ መሪዎች ለፈጸሙት የጦር ወንጀል ለፍትሕ መቅረብ አለባቸውም ያለው ኤምባሲው ማንም ሀገር በየትኛውም አቅጣጫ ጥቃት ሲደርስበት በዝምታ እንደማይመለከት አስገንዝቧል፡፡

በትግራይ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር መነሻ በማድረግ መንግሥት በሰብዓዊነት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉን የጠቀሰው ኤምባሲው አሸባሪው ቡድን ግን ይህንን አማራጭ ባለመቀበል ወደተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት በመሰንዘር ጉዳዩ እንዲባባስ እያደረገው ነው ብሏል፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ጸሐፊዋ አሸባሪው ቡድን ወደ አጎራባች ክልሎች የሚያደርገውን ተስፋፊነት ከማንሳት ይልቅ አሸባሪውን ሕጋዊ በማስመሰል በኢትዮጵያ ላይ ምክንያታዊ ማዕቀብ እንዲጣል መሻቷን ኮንኗል፡፡

ኤምባሲው እንዳለው የወጣው ጽሑፍ እውነታን የማያሳይና በኢትዮጵያ ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫና እንዲፈጠር የሚገፋፋ ነው ሲል በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleከተቋቋሙበት የሰብዓዊ ሥራ ዓላማ ውጭና የሀገርን ጥቅም በሚጻረር መልኩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶች ታገዱ፡፡
Next articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሕዳሴ ግድብ 103 ቢሊዮን ብር ወጭ ማድረጉን አስታወቀ።