
በኢትዮጵያ እና አልጀሪያ መካከል ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ግንኙነቶችን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሳድግ የታመነበት የቢዝነስ ካውንስል ተመሠረተ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ካውንስሉ በሁለቱ ሀገራት የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች መካከል በበይነ መረብ አማካኝነት በተደረገ የፊርማ ሥነ-ሥርዓት መመሥረቱን የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
በኢትዮጵያ እና አልጀሪያ ጠንካራ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መኖሩን ያስታወሱት የአልጄሪያ የንግድ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ከማል ራዚግ ይህንን ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት የሚመጥን የኢኮኖሚ ልውውጥ እንዲኖር በመንግሥታቸው በኩል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በዚህም የሁለቱን ሀገራት የቢዝነስ ማኅበረሰብን ከማቀራረብ አኳያ በአልጀርስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና አዲስ አባበ የሚገኘው የአልጄሪያ ኤምባሲ እያከናወኑ የሚገኙትን ተግባራት አመስግነዋል።
የቢዝነስ ካውንስሉ መመሥረት የንግድ፣ ኢንቨስትመንት ልውውጥን እንደሚያሳድግ እምነታቸው መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በአልጄሪያ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በበኩላቸው፣ በሁለቱ ሀገራት በሚገኙ የቢዝነስ ማኅበረሰብ መካከል የተለያዩ የንግድ እና ኢንቨስተመንት ልውውጦችን ለማከናወን ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል።
ይህን ፍላጎት ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየርም የቢዝነስ ካውንስሉ መመሥረት አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሁለቱ ሀገራት የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች የቢዝነስ ካውንስል መመሥረቻ ሰነድ እንዲፈረም ላሳዩት ከፍተኛ ተነሳሽነት ምስጋና አቅርበዋል።
የቢዝነስ ካውንስሉ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ልውውጥ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንዲሁም የልውውጥ መስኮችን ለመለየት የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ነው አምባሳደር ነብያት ጌታቸው የገለጹት።
በአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሊና በበኩላቸው፣ በቅርቡ አዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ያደረጉት የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራማታን ላማምራ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ሁለንታናዊ የኢኮኖሚ ግንኙነቶችን ለማሳደግ የሚያስችሉ ጉዳዮችን በተመለከተ ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
