
ለህልውና ዘመቻ በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን በአንድ ጊዜ ብቻ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ቡድንን በጦር ግንባር እየደመሰሰ ለሚገኘው ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ድጋፍ የሚውል ሀብት ለመሰብሰብ በተዘጋጀ መርኃ ግብር በአንድ ጊዜ ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተሰበሰበ፡፡
በፍኖተ ሰላም ከተማ የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር በጋራ በመተባበር ለህልውና ዘመቻ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን መርኃ ግብር አካሂደዋል፡፡ በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን መርኃ ግብር የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሃይማኖት ተቋማት እና ሌሎችም ተሳትፈዋል፡፡
“አሸባሪው ትህነግ ከምስረታው ጀምሮ አማራን ጠላት ያደረገ፣ ኢትዮጵያዊ መንፈስና ሥነ ልቦና የሌለው አሸባሪ ቡድን በመሆኑ መጥፋት አለበት” ያሉት የመርኃ ግብሩ አስተባባሪ የፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዓለማየሁ ሽፈራሁ ናቸው፡፡ ለህልውና ዘመቻው ገቢ ለማሰባሰብ የንግዱ ማኅበረሰብ ከመቸውም ጊዜ በላይ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
“አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያን ለመበታተን እየሠራ ያለ በመሆኑ ቡድኑ እስኪደመሰስ ድረስ ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገር የህይወት መስዋእትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል” ብለዋል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ እስካለ ድረስ አይደለም ነግዶ ማትረፍ በሰላም ወጥቶ መግባት ስለማይቻል የንግዱ ማኅበረሰብ ድጋፋን ማጠናከር አለበት ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ቀደምት ባለታሪክ ሀገር ናት፤ በተለያየ ጊዜ ሀገሪቱ እንድትበታተን ተሞክሮ ያልተሳካና ወራሪን አሸንፋ አሳፍራ የምትመልስ ሀገር ናት ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪና የቴሌቶኑ ተሳታፊ አቶ በፍቃዱ ዲሳሳ ናቸው፡፡
አሸባሪው ትህነግ ሀገርን ለማፍረስ ማሰቡ “ቅዠት ነው” ሲሉ ገልጸውታል፡፡
በየደረጃው ያለው የጸጥታ ኀይል ለሀገር ደኅንነት የህይወት መስዋእትነት እየከፈለ ነው ያሉት አቶ በፍቃዱ የንግዱ ማኅበረሰብና መላው ሕዝብ ሀብት በማሰባሰብና በተለያየ ድጋፍ ከጸጥታ ኀይሉ ጎን መቆም ይገባል ነው ያሉት፡፡
ሌላዋ የፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪና የቴሌቶኑ ተሳታፊ ወይዘሮ ሙሉጎጃም አስፋው በበኩላቸው የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ ለመመከት ከስንቅ ማዘጋጀት ጀምሮ በተለያዩ ድጋፎች እየተሳተፍን ነው ብለዋል፡፡ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ግንባር ለሚፋለመው የጸጥታ ኀይል ሀብት በማሰባሰብ የንግዱ ማኅበረሰብ ያሳዬው አጋርነት ያመሰገኑት ደግሞ የፍኖተ ሰላም ምክትል ከንቲባ ደሳለኝ ካሳሁን ናቸው፡፡ ነጋዴው በተለያዬ ጊዜ በአይነትና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ሲያደረግ መቆየቱን የገለጹት ምክትል ከንቲባው በተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ከንግዱ ማኅበረሰብ ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት በአንድ ቀን ብቻ በካሽ እና ቃል የተገባ 4 ሚሊዮን 663 ሺህ 216 ብር መሠብሰቡን ገልጸዋል፡፡
የአሸባሪውን ወረራ ተከትሎ መንግሥት የክተት ጥሪ ማስተላለፉን ያስታወሱት አቶ ደሳለኝ ግንባር መዝመት የምንችል በመዝመት፣ ሌላው ማኅበረሰብ ደግሞ ሀብት በማሰባሰብ ከተጋረጠብን የህልውና አደጋ ራሳችንን እንታደግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፍኖተ ሰላም ከተማ አስተዳደር ለህልውና ዘመቻ ድጋፍ እስካሁን ድረስ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከመንግሥት ሠራተኛውና ከሕዝቡ በአይነትና በጥሬ ገንዘብ ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሀብት መሰብሰቡን ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ይርጋ – ከፍኖተሰላም
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
