
“ህልውናችንን ለማስጠበቅ የገባንበት ጦርነት የማብቂያ ዳርቻው አሸባሪው የትህነግ ቡድን የትግራይ ክልልን ጨምሮ ከመላው የኢትዮጵያ ምድር ተጠራርጎ ሲወገድ ብቻ ነው” የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ውስጥ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ፤ ከነዚህ ውስጥ 2 መቶ ሺህ ያህሉ አሸባሪው ትህነግ በከፈተው ቀጥተኛ ጦርነት ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ናቸው ብለዋል፡፡ ቀሪዎቹ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ተፈናቃዮች ደግሞ አሸባሪው ትህነግ ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ በትግራይ እና ከትግራይ ክልል ውጭ በሚኖሩ አማራዎች ላይ በተዘዋዋሪ መልኩ ባስፈጸማቸውና በቀጥታም በተሳተፈባቸው ጥቃቶች ምክንያት ከእርሻ እና ከመኖሪያ አካባቢያቸው ያሳደዳቸው እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ተፈናቃይ ወገኖችን በህይወት ለማቆየት በወር ከአንድ መቶ ሀምሳ ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
አቶ ግዛቸው እንደተናገሩት በህወሃት የሽብር እና የሴራ ወለድ ጥቃቶቹ ምክንያት በተፈናቃይ ቤተሰቦች ላይ የተፈጸሙት አሰቃቂ ግድያዎች፤ የአካል መጉደል እና የንብረት ውድመት የሰው ልጅ አዕምሮ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ መሆናቸው ነበር፡፡
“ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በተከታታይ ሲፈጸሙ “ለመስማትም ኾነ ለማየት” ተስኗቸው የነበሩ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ” ግብረ-ሠናይ” ነኝ ባይ ፌዘኛ ተቋማት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ምድር በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ሁሉ መሃንዲስ በሆነው የህወሃት የሽብር ቡድን ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ ሲጀምር “ለመስማትም፤ ለማየትም ሆነ ተናግሮ ለማውገዝ ዱዳ ሆነው በነበሩበት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሥም የባጡንም የቆጡንም ማንጎራጎር የሙሉ ግዜ ሥራቸው አድርገውታል” ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም እንዲሉ ዓይን ባወጣ የሐሰት መረጃ ተበዳይን ነጋ ጠባ በመክሰስ ተጠምደዋል፤ ይህ ኢፍትሐዊ ድርጊታቸው የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪነትን ትርጉም እስክንጠራጠረው ድረስ ስያሜውን እንጂ ግብሩን ያልተላበሱት ” ግብረ ሠናይ” ድርጅቶችና ተቋማት ግባቸው ምን እንደሆነ ለመገንዘብ ችለናል ነው ያሉት፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ስለ እርዳታ ለመነጋገር ስለ ድንበር አከፋፈትና እና የሕግ አስከባሪ ኃይሎች ስምሪት ዙሪያ መስማማትን ቀብድ አድርጎ መሟዘዝ የ”ሥመ- ግብረ ሠናይ ተቋማቱን” ስውር ፍላጎት በግልፅ ያስረዳል ብለዋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ ያለ እረፍት ሲፈጽም የነበረውና እየፈፀመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች የግፍ ጽዋ ሞልቶ ከፈሰሰ በኋላ እንኳን ዛሬም እየፈጸማቸው የሚገኙት ወረራዎች፣ ግድያዎች፤ ንጹሐንን አፍኖ የመውሰድ፤ የዝርፊያ እና የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች እንዳልተቋረጡም አብራርተዋል፡፡
የአሸባውን ትህነግ ሞልቶ የፈሰሰ አሸባሪነት በገሃድ የሚያውቁት “የፌዘኞቹ ግብረ-ሠናይ ተቋማት” ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያደረ እንጉርጉሮ ግን ዛሬም አልተለወጠም፤ ቅኝቱ ባለተቀየረው የፌዘኛ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንጉርጉሮ መንፈሳችን አይታወክም፤ ከሽብር ድርጊቱ ባልታቀበው የትህነግ ቡድን የደቀነብንን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ከጀመርነው ትግልም አንዝልም፤ ወደ ኃላም አንመለስም ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ተቋማት ቁማር ከትህነግ የጥፋት ግልቢያ ጋር ያለውን ጥልፍልፍና ውስብስብ ችግር ተረድተን የጀመርነው ተጋድሎ ሣንጨርስ የማናቆመው ሁነኛ ጉዳያችን መሆኑን ያረጋግጣል ነው ያሉት፡፡
“ላንጨርስ አልጀመርነውም፤ እንዲህ ያለውን ትግል ከአባቶቻችንም አልተማርንም፡፡ ለዚህ ለሕዝባችን ካንሰር የሆነው አሸባሪ የትህነግ ቡድን የሚተኛ የሥነልቦና ውቅር ያለው ሕዝብም የለንም። ስለሆነም ህልውናችንን ለማስጠበቅ የገባንበት ትግል መቆሚያ ዳርቻው፤ የትህነግ የሽብር ቡድን የትግራይን ክልል ጨምሮ ከመላው የኢትዮጵያ ምድር ተጠራርጎ ሲወገድ ብቻ ነው” ብለዋል፡፡
እንደመላው ኢትዮጵያውያን ሁሉ የአማራ ሕዝብም ፖለቲካዊ-ካንሰርን ተሸክሞ ለመኖር አይፈቅድም ያሉት አቶ ግዛቸው ትእግስቱም እዝነቱም የለውም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ከተውጣጡት የሁሉም ክልሎች የልዩ ኃይልና ሚሊሻ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ እየፈጸመ የሚገኘው አሸባሪውን ቡድን የመደምሰስ ተጋድሎ የትግላችን ማቆሚያ ትህነግን ነቅሎ ወይም የጋራ ጠላታችንን በማውደም ብቻ የሚቋጭ መሆኑን አስረግጦ ያሳያል ብለዋል፡፡
በአውደ ውጊያው ውሎም የጠላት ቡድን በሁሉም ግንባሮች አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በርካታው ተገዶ ወደ ጦርነቱ የተሰለፈው የጠላት ቡድን አከርካሪውን እየተመታ ባለበት እየተቀበረ ይገኛል ነው ያሉት።
“ህልውናችንን የማስቀጠል ዘመቻ ሳንጨርስ የማናቆመው በከፍተኛ ወኔና እልህ የምንፈፅመው የታሪካችን አካል ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
