
በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ዙሪያ በተደረገ ውይይት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ7 ነጥብ 3 ሚለዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች ከኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ማኅበር የአመራር ቦርድ አባላትና ዲፕሎማቶች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ዙሪያ በተረገ ውይይት ለኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ከ7 ነጥብ 3 ሚለዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ፡፡
በውይይቱ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎና በዱባይና ሰሜን ኤመሬትስ የኢፌዴሪ ቆንስላ ጄኔራል አምባሳደር እየሩሳሌም አምደማሪያም፣ የዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ማኅበር የአመራር ቦርድ አባላትና ዲፕሎማቶችም ተሳትፈዋል።
በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች ቆንስላ ጄነራል ጽሕፈት ቤት በተካሄደው ውይይት ከሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ተቀናጅተው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጦርነት መክፈታቸው የተብራራ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የሕዝቦቿን ህልውና ለማስከበር ሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ተገልጿል።
ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እየተደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በአቡዳቢ እንዲሁም በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ማኅበራት የአመራር ቦርድ አባላት ሌሎች የዳያስፖራ ማኅበራትንና ሀገር ወዳድ የዳያስፖራ አባላትን በማስተባበር ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንዳለባቸው አምባሳደሮቹ አሳስበዋል።
የዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ማኅበር የአመራር ቦርድ አባላት ኢትዮጵያን ለማዳንና በሚደረገው እንቅስቃሴ የወገንንና የሀገርን ጥሪ በመቀበል ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ድጋፍ ይሆን ዘንድ በማኅበሩ ስም 500 ሺህ ድርሃም ለመለገስ ወስነዋል።
የአቡዳቢ የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ማኅበርም ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስድ ይጠበቃል።
ከዚህም በተጨማሪ በአቡዳቢ የኢፌዴሪ ኤምባሲና በዱባይ የኢፌዴሪ ቆንስላ ጄኔራል ጽሕፈት ቤት የሚገኙ ዲፕሎማቶች በነፍስ ወከፍ ከ1ሺህ እስከ 2 ሺህ ዶላር በማዋጣት በጠቅላላው አንድ ነጥብ 3 ሚሊዮን የለገሡ ሲሆን፣ ሠራተኞችም እንደየገቢያቸው ሁኔታ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራው ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
