
“ኢትዮጵያን ከአሁናዊ ችግሯ ለማውጣት ለሠራዊቱ ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት እና በመተባበር ሊሰራ ይገባል” ደበበ እሸቱ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የተውኔት፣ የፊልም፣ የራዲዮና የቴሌቪዥን ድራማዎች፣ የጋዜጠኝነት፣ የተርጓሚነትና የደራሲነት ሙያዎች ባለቤት የሆነው አንጋፋውና ሁለገቡ የኪነ ጥበብ ሰው ደበበ እሸቱ ከኢትጵያ ስመ ጥር ከያኒያን ግንባር ቀደም ነው።
በኢትዮጵያ በተካሄደው የ1997ቱ ምርጫ ወደ ፖለቲካው ዓለም ገብቶ ባሳለፈው እስር የወያኔን የሽብር ቡድን ጭካኔና ተንኮል በውል የተረዳው አንጋፋው ከያኒ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርጓል።
አሜሪካን ጨምሮ የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ያለው የተዛባ እሳቤና ጫና ከምን የመነጨ ይሆን ለሚለው ሃሳብ ደበበ ‘የኢትዮጵያ ቅኝ አለመገዛትና ድል ማድረግ ሁሌም ነጮችን ያናድዳቸዋል’ ይላል።
ለዚህም ከኢትዮጵያ ታሪክና ማንነት ጋር የሚቃረንና ተላላኪ ስርዓት እንደሚደግፉ በመግለጽ ከጫካ ጀምሮ በዕርዳታ ስም የጦር መሳሪያ በመርዳት ለስልጣን ያበቁትን አሸባሪውን የሕወሃት ቡድን ማሳያ ይጠቅሳል።
በርካታ የአሜሪካ ባለስልጣናት ፀረ ኢትዮጵያው ከሆነው የሕወሃት ቡድን ጋር ያላቸው ዝምድናም ኢትዮጵያን ከመበቀል የመነጨ እንደሆነ ይገልጻል።
ኢትዮጵያ አሜሪካ ከመፈጠሯ በፊት የነበረች ሉዓላዊት አገር፣ ጥንታዊ ሃይማኖትና እሴት ያለው ሕዝብ ባለቤት በመሆኗ ይህች አገር እንድታድግ እንደማይፈልጉም ይገልጻል።
ለዚህም አንዱ ወያኔዎች ሆነ ብለው ያጓተቱት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መፋጠኑ ከጥንምትም ግብጽና ቅኝ ገዥዎቿን በማበሳጨቱ ኢትዮጵያ ላይ መልከ ብዙ ጫና ማድረግ እንደፈለጉ ይናገራል።
ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማስታረቅ የምዕራቡ ዓለም ተጽዕኖ “ፈጣሪ ነን” የሚሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ያልቻሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዕውን አድርገው የሠላም ኖቬል መሸለማቸውም ያበሳጫቸዋል ይላል።
ደበበ ነጭ ሕንዶችን በአጥር ከልላ ያስቀመጠች፣ በቀለም ለይታ አደባባይ ላይ የገደለች፣ በተለያዩ አገራት ዘር ማጥፋት የፈጸመችው አሜሪካ ስለ ሠብዓዊ መብት ማውራት አይገባትም ነበር ባይ ነው።
ይህም ብቻ ሳይሆን አሸባሪው የህወሓት ቡድን ማይካድራን ጨምሮ የዘር ማጥፋት ሲፈፅም እንዲሁም ህጻናትን ለጦርነት በማሰለፍ ዓለምአቀፍ ህግ ሲጥስ አሜሪካና ባለስልጣናቷ ዝምታን መርጠዋል ብሏል።
በትራምፕ መሸነፍ የበርካታ ዜጎች ሞት ያስተናገደችው አሜሪካና አጋሮቿ የዘንድሮው አገር አቀፍ ምርጫ በሠላም እንደማይከናወን ቢያሟርቱም ምርጫው ያለምንም ችግር መጠናቀቁን ጠቅሷል።
የዚህ ሁሉ መነሻው ለዴሞክራሲና ሠብዓዊ መብት በመቆርቆር ሳይሆን ለአሜሪካ መንግስት ተላላኪ የሚሆን ስርዓት ለመፍጠር በማለም እንደሆነ ገልጿል።
የወያኔ ስርዓት የሚያስፈጽመው በአሜሪካ ጥቅምና ጥያቄ የተቃኘ ዕቅድና ፕሮግራም እንደነበር የገለጸው ከያኒው፤ ዳሩ ግን የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን ባለማድረጋቸው ጫናው እንደበረታ ይናገራል።
እናም የምዕራቡ ዓለም ጫና ማብዛት ተላላኪና ዓላማቸውን የሚያስፈጽም የኢትዮጵያ መንግስት እንዲፈጠር ከመፈለግ የመነጨ ነው ብሏል።
በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን በኢትዮጵያዊያን ትግል ተገርስሶ አዲስ ለውጥ በመምጣቱ የአሜሪካ ከሽብር ቡድኑ ጋር የማስታረቅ ፍላጎትም ተቀባይነት እንደሌለው ተናግሯል።
ኢትዮጵያን ከአሁናዊ ችግሯ ማውጣት ለሠራዊቱ ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት እና መተባበር ሊሰራ እንደሚገባው ተናግሯል። ዘገባው የኢብኮ ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
