ʺላትችሏት አትነቅንቋት ላታስቆሟት አትጎትቷት”

173

ʺላትችሏት አትነቅንቋት ላታስቆሟት አትጎትቷት”

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ገፍተው አጠነከሩን፣ ጎትተው አፈጠኑን፣ ጠብ ጭረው አዋደዱን፣ ጦር ጀምረው አንድ አደረጉን፡፡ ሲገፉህ ከተጠነከርክ፣ ሲጎትቱህ ከፈጠንክ አንተ ብልህ ነህ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሥሪት ጠላት ከሚቀምረው ቀመር፣ ለማፍረስ ከሚያሰምረው መስመር፣ ከሚለካው ድንበር ሁሉ የበለጠ ነው፡፡ እርሷ የምትጠበቀው ልጆቿ አብዝተው በሚወዱት፣ እርሱም በሚወዳቸው ኃያል አምላክ ነው፡፡ የጦር ነጋሪት ከሚጎስሙት ሳይታክቱ ለፈጣሪያቸው ምልጃ የሚያቀርቡት ይልቃሉ፡፡ እነርሱ የምድሩ ክፋት እንዲጠፋ፣ የሰማይ በረከት ደግሞ እንዲሠፋ ያደርጋሉና፡፡

ዓለማት ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ይመለከታሉ፣ በውስጧ ያለውን ነገር ሁሉ ያገኙ ዘንድ ይሻሉ፣ በምስጢራዊነቷ፣ በቀደምትነቷ፣ በአንድነቷና በአይደፈሬነቷ ይከፋሉ፣ እንቅልፍ ያጣሉ፣ ኢትዮጵያ ግን ዓለማትን አታየቸውም፡፡ ለምን ካሉ በእነርሱ ያለው ሁሉ ከዘመን ቀድሞ በእርሷ ነበር፣ አለ፣ ይኖራል፣ በእርሷ ያለው ግን በእነርሱ ላይ የለም፡፡ ኢትዮጵያ የምታዬውና እጇን የምትዘረጋው ወደፈጣሪዋ እንጂ ወደ ማንም አይደለም፡፡

ለምድር የተሰጡ በረከቶች፣ በሰማይ ላለው አምላክ የሚቀርቡ ምስጋናዎች ሁሉ በኢትዮጵያ አሉ፡፡ ሳይታጎሉ ይደርሳሉ፡፡ ለምስክር፣ ለክብር፣ ለፍቅር፣ ለምስጢር የተፈጠረች ውብ ምድር፡፡ የጌታ ዓይኖች ያለ ማቋረጥ ይመለከቷታል፣ የጌታ ጀሮዎች ምልጃዎቿን ይሰሟታል፣ የጌታ እጆች ምድሯን ይባርኳታል፣ የጌታ አገልጋዮች ዙሪያ ገባዋን ይጠብቋታል፣ እርሱን የሚፈሩትና የሚያከብሩት በምድሯ የተፈጠሩ፣ ለክብሯና ለፍቅሯ የሚኖሩ ጀግኖች አለን ይሏታል፡፡

ዓለማት ትናንትና ዛሬ የውስጧን ለመውረስ፣ አንድነቷንም ለማፈራረስ ይመኟታል፣ ነገ ግን ተስፋና መጠለያ ያደርጓታል፡፡ እርሷ በጥበብ የተሰራች፣ ከዓለት ላይ የፀናች፣ ከምንም እና ከማንም በልጣ የተጠበቀች ናትና ችሎ የሚገፋት፣ ገፍቶ የሚጥላት፣ ኾኖለት ከክብሯ የሚያወርዳት የለም፡፡ እርሷ የዓለም መሠረት ናት፣ መሠረት ደግሞ ጠብቆ ይኖራል እንጂ ጣሪያና ግድጋዳውን ጥሎ አይወድቅም፣ ዘመነ ፍፃሜ ደርሶ መሠረቷ ከለቀቀች ዓለማትም እንዳልነበር ይኾናሉ፡፡ ጀማሪዋ ሳትኖር ተከታዮቿ ሊኖሩ አይችሉምና፡፡

የነኳት ሁሉ ያልቃሉ፣ የገፏት ሁሉ ይወድቃሉ፣ የወደዷትና ያከበሯት ይከብራሉ፣ ይደምቃሉም፡፡ የጠላቶቿ ክፋት ከኢትዮጵያዊያን አንድነትና እሴት ሁሉ በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡ የእነርሱን አንድነት፣ እሴትና የጸና እምነት የጦር መሳሪያ አይቆራርጠውም፣ የምድር ኃይል አያሸንፈውም፣ ማዕበል አይገፋውም፣ ነፋሳት አያጠፉትም፣ የጨለማ ድቅድቅ አይጋርደውም፡፡ እሴታቸው አንድነትን፣ አንድነታቸው አሸናፊነትን፣ ሃይማኖታቸው በረከትን፣ በረከታቸው ጽናትን፣ ጽናታቸው የበላይነትን እያመጣላቸው ይኖራሉ እንጂ፡፡

ማን አለ እንደርሷ ኾኖ የተፈጠረ ሠንደቁ በሰማይ ላይ የተኖረ፣ ጸጋ ሀሉ የተቸረ፤ አምላክ ሰውና መላእክት በአንድነት የሚጠብቋት፣ ጠቢባን የሚያደንቋት፣ ሊቃውንት የሚቀኙላት፣ ነብያት የተነበዩላት፣ የራቋት የሚናፍቋት፡፡ የጥበብ ሁሉ መሶበ ወርቅ የሆነችው ኢትዮጵያ በየዘመናቱ አያሌ የፍስሃና የመከራ ዘመናትን አሳልፋለች፣ ጠላቶቿ እርሷን ከማስገበርና ከመመዝበር ካላቸው ከንቱ ምኞት የተነሳ በየዘመናቱ ድንበሯን መርገጣቸው አልቀረም፡፡ ታዲያ በከንቱ ምኞት መጥተው ድንበሯን የጣሱ በዚያው ሲመለሱ፣ ካለበለዚያም ወደ መጡበት ወደ አፈር ሲመለሱ፣ በፍቅር የመጡት ደግሞ ከበረከቷ እየተቋደሱ ነው የኖሩት፡፡

ኢትዮጵያዊያን ስለ ፍቅር እጅ ይነሳሉ፣ ስለ ጥል ነፍጥ ያነሳሉ፣ አንገት ይበጥሳሉ፣ እጃቸው ለፍቅርም ለጦርም የተመቸ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ለፍቅርም ኾነ ለጦር የተጓዘ ሁሉ የመልስ የጉዞ ታሪኩ ተሸንፌያለሁ የሚል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን አሸነፍኳቸው ብሎ የመልስ የጉዞ ታሪክ የጻፈ የለም፤ ወደፊትም አይኖርም፡፡ ከሀገሩ ሲነሳ ወዮላት ለዚያች ሀገር ብሎ የተነሳው ጠላት ሁሉ ሲመለስ ወዮልን ለእኛ ፣ ለላኩን ምን እንገር፣ የኢትዮጵያ አፈር የበላቸውን ወገኖች እናት ስናገኝ ምን እንመልስ እያሉ በሀዘን ይመለሳሉ፡፡ ኢትዮጵያን ሊያጠቃ የመጣ ሁሉ እየተደሰተ መጥቶ እያለቀሰ ይመለሳል፡፡

ብዙ ይዘው ኢትዮጵያንም ለመያዝ የጣሩት በእርሷ ምክንያት የያዙትንም አጥተዋል፣ በኢትዮጵያ ምክንያት ገናንነታቸው ተንኮታኩቷል፣ ያጨለሙት ዘመን በብርሃን ተተክቷል፣ ጎዳናዎቻቸው በሀዘን ተሞልተዋል፣ የጦር መሪዎቻቸው ሁሉ አንገታቸውን ደፍተዋል፣ በዓለም ፊት አፍረዋል፣ ኢትዮጵያዊያን ግን ከማማው ላይ ኾነው ኮርተዋል፣ የብርሃንን መንገድ ለዓለም አሳይተዋል፡፡ ዓለምም ደንግጣለች፣ የጭቁኖች ፀሐይ ያለ ምንም ከልካይ ወጥታለች፣ ወደ ነጭ ያዘነበለችው የዓለም ሚዛን እኩል ሆናለች፣ በኢትዮጵያዊያን ምክንያት በግዞት የታሰሩ እጆች ተፈትተዋል፣ የንጹሐን ማጎሪያ የነበሩ እስር ቤቶች ተከፍተዋል፣ በማንነታቸው ሲያፍሩ የነበሩ ጥቁሮች ሁሉ ኮርተዋል፣ አንገታቸውን አቅንተዋል፣ ማንነታቸውን አስከብረዋል፡፡

ዘመን ዘመናትን አልፎ ኢትዮጵያ ተካታዮቿን እያሰለጠነችና እየታዘበች ቀጥላለች፡፡ ይህች ውብ ምድር እንደ አሳለፈችው ዘመን ሁሉ ዛሬም ሌላ ችግር ገጥሟታል፡፡ ዳሩ ለችግር አትወድቅም፣ ለክፉዎች አትጨነቅም፣ በብልሃት ታልፈዋለች እንጂ፡፡

ኢትዮጵያዊያን ችግር ሲገጥማቸው አንድነታቸው የበለጠ የሚመጣ፣ ኃያልነታቸው ገፍቶ የሚወጣ ነው፡፡ ሀገር ተነካች፣ ወንዜ ተደፈረች ያሉት ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ሊጠብቋት፣ ለክብሯ ሊሞቱላት፣ ለልዕልናዋ ሊዋደቁላት ከዳር ዳር መነቃነቅ ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ችግር ሲገጥመው የሚያብር እንጂ የሚሸበር አይደለም፡፡

ትናንት በራስ ትጥቅና ስንቅ ዘምተው፣ የጠላትን ወራሪ ድባቅ መትተው፣ የአፍሪካን የነጻነት ጀንበር በዓድዋ ላይ አብርተው የተመለሱት ኢትዮጵያዊያን ልጆች ዛሬም ሀገሬን የሚደፍራት፣ ክብሯን የሚነካት ስሟን የሚያጎድፋት የለም እያሉ ነው፡፡ የቀደመው ገናና ታሪክ እየገፋቸው፣ የአባቶችና የእናቶች የአንድነት ድምጽ እየጠራቸው፣ ወኔና ጀግንነታቸው እያጀገናቸው፣ ታሪክ ሰሚ ብቻ ሳይሆኑ ታሪክ ሰሪም ለመሆን እየተጠራሩ ነው፡፡ የማይነካውን መንካት፣ በኢትዮጵያ መምጣት የቀፎውን ንብ ይቀሰቅሳል፣ የአንበሳውን ቁጣ ያስነሳል፣ ንቡ ከገነፈለ፣ አንበሳው ካገሳ ወዲያ ደግሞ መካች አይገኝለትም፣ በንቡ መነደፍ፣ በአንበሳው መሰልቀጥ አይቀሬ ነው፡፡

መሬቷ ያበቀለቻቸው እንክርዳዶችና ከወሰኗ ማዶ የመጡ ጠላቶች ኢትዮጵያዊያንን በታተንናቸው፣ አንድነታቸውን ቀማናቸው፣ አቅም አሳጣናቸው፣ ግርማቸውን ወሰድንባቸው ሲሉ በአራቱም ንፍቅ ያሉት፣ ከምድሯ ርቀው የሚኖሩት ከአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ ግርጌ ቆመው ቃላቸውን አደሱ፣ እንባቸውን አፈሰሱ፣ ኢትዮጵያን የነካ ወዮለት ብለው ተነሱ፡፡ የደከመ የመሰለው አንድነት፣ የደበዘዘ የመሰለው ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ ወጣ፡፡ ወታደር ኾኜ ልጠብቅሽ፣ ከሰንደቅሽ በፊት እኔን ያድርግልሽ የሚለው በዛ፡፡ ለእናት ሀገር ጥሪ ሁሉም ጀግና ኾኖ ሀገሩን ለመጠበቅ ተመመ፡፡

አሁን እናት ኢትዮጵያ ድምጿን ከፍ አድርጋ ተጣርታለች፣ ልጆቼ የቀደሙትን ታሪክ አደራ፣ በልጆቼ አላፍርም፣ በጠላትም አልደፈርም ብላለች፡፡ የሀገር ጥሪው የደረሰው፣ የእናት ፍቅር አንጄቱን ያላወሰው፣ ወኔ የቀሰቀሰው ሁሉ ቃሏን አደራውን ሊወጣ ከቤቱ ተነስቷል፤ ወጣቱ ለመዝመት፣ ሽማግሌው ለጸሎት፣ ሌላው ለስንቅና ለትጥቅ ዝግጁ ነው፡፡ ʺታዲያ እንቢ ካለ ምክር ካልመለሰው፣ መጥቶ እጄን ይቅመሰው” የሚለው በዝቷል፡፡ ከመንደር ይልቅ ለሀገር፣ ከእኔ ይልቅ ለእኛ የሚለውም ተበራክቷል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ጽናት፣ ኢትዮጵያዊነት አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነት ምስጢራዊነት ኢትዮጵያዊነት የችግር መፍቻ ምስጢር፣ ኢትዮጵያ በጠላቶች አዕምሮ የማትመረመር ድንቅ ሀገር ናትና ጠላቶች የጠበቁት ሳይሆን የፈሩት ኾነባቸው፡፡

ኢትዮጵያዊነት እያሸነፈ፣ የጠላት ዕቅድ እየከሸፈ እየሄደ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከክብሯ ማውረድ፣ ኢትዮጵያዊያንን ማዋረድ አይቻልም፡፡ ላትችሏት አትነቅንቋት፣ ላታስቆሟት አትጎትቷት፣ እርሷ በእናንተ አቅም የምትፈርስ፣ በእናንተ እርኩሰት የምትረክስ ሀገር አይደለችም፡፡ እርሷ ከተቀደሱት የተቀደሰች፣ ከተከበሩት የተከበረች፣ ከምንም እና ከማንም ከፍ ያለች ናት፡፡ እርሷን ለመጉዳት ከመቀመር፣ ለሺህ ዘመናት የቆዬውን ታሪኳን መመርመር ይሻላል፡፡ ያን ጊዜ እውነታው ይገለጥላችኋል፣ ምስጢሩ ይገባችኋል፡፡ እውነቱ ሲገለጥላችሁ ምስጢሩ ሲገባችሁ ደግሞ የኢትዮጵያ ተከታዮች፣ ወዳጆች፣ የኢትዮጵያ አምላክ ተማጻኞች ትኾናለችሁ፡፡ ኢትዮጵያን መውደድ እንጂ ማዋረድ አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያን አክብር፣ ያን ጊዜ ትከብራለህ፣ ኢትዮጵያን ጠብቅ ያን ጊዜ ትጠበቃለህ፣ ኢትዮጵያን ውደድ ያን ጊዜ ትወደዳለህ፣ ኢትዮጵያን የጠላህ ቀን ግን ትጠፋለህ፡፡

በታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለሕልውና ዘማቾች የስንቅ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡
Next article“የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከጠላታችን ትህነግ ጋር በምናደርገው ፍልሚያ እስከ መጨረሻው ከጎናችን እንድትሆኑ እጠይቃለሁ” የመከላከያ ሚኒስቴር የውጪ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ቡልቲ ታደሰ