
የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለሕልውና ዘማቾች የስንቅ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ የሚኖሩ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ከ100 ሺህ ብር በላይ ግምታዊ ያለው ስንቅ ለሕልውና ዘማቾች በታላቁ ሰላም በር መስጂድ እያዘጋጁ ነው፡፡
አስተያዬታቸውን የሰጡ እናቶች እንዳሉት አሸባሪው የትህነግ ቡድን አረም ነውና ነቅሎ መጣል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ልዩነት ሳይገድበው በጋራ መታገል አለበት ብለዋል።
አሸባሪው ትህነግ እድሜያቸው ያልደረሰ ሕጻናትን ለጦርነት ማሳለፉ እንዳሳዘናቸውም እናቶች ተናግረዋል፡፡
ሕጻናት መማር ሲገባቸው ለጦርነት ማሰለፉ አሳፋሪ በመሆኑ አሸባሪውን ቡድን ማስወገድ ሀገሪቱን ከመታደግ ባለፈ የትግራይን እናቶችና ሕጻናትን ጭምር ነጻ ማውጣት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ሀገራችንን ከጽንፈኛው ቡድን ለመታደግ ግንባር በመዝመት ውድ ሕይወታቸውን እየሰጡን ነው፤ እኛም የኋላ ደጀን በመሆን ስንቅ እያዘጋጀን ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ድል እስክትቀዳጅ ድረስም የኋላ ደጀን ሆነው እንደሚዘልቁ ነው አስተያዬት ሰጪዎቹ የተናገሩት፡፡ የተዘጋጀውን ስንቅ ቦታው ድረስ ሄዶ እስከማስረከብ ድረስ ያላቸውን ዝግጁነትም ገልጸዋል፡፡
የባሕርዳር ከተማ ዑለማ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሸህ ሑሴን ሐሰን የሀገር ሕልውናን ለማስጠበቅ ሙስሊሞች የሚጠበቅባቸውን እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡
ወጣቶች ግንባር ድረስ በመሄድ፣ አቅም ያለው በገንዘብ፣ አዛውንቶችና ዑለማዎች ደግሞ ጸሎት በማድረግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በመጣስ ሴቶችን፣ አዛውንቶችንና ሕጻናትን ለጦርነት ሲያሰልፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በዝምታ ማለፉ እንዳሳዘናቸውም ተናግረዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የውጪ ኀይሎችና የሀገር ውስጥ ባንዳዎች ጋብቻ መፈጸማቸውን ያሳያል ብለዋል፡፡
በሀገር ውስጥ ያለው ባንዳ የትም አይደርስም ያሉት ሸህ ሁሴን በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሚጥሩ አካላት አቋማቸውን ሊፈትሹ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ ጦርነቱ እስኪያበቃ ድረስ ሁሉም አካል በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በጸሎትና ግንባር ድረስ በመሰለፍ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ኀላፊና የህልውና ዘመቻው የስንቅ ዝግጅት አስተባባሪ አምሳል ካሰው ዘመቻው ከተጀመረ አንስቶ የስንቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የከተማዋ ሙስሊም ማኅበረሰብ ድጋፍ የዚህ አካል እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለመከላከያ ለልዩ ኀይልና ለሚሊሻ የስንቅ ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
እስካሁን ድረስ ከ700 ኩንታል በላይ የተለያዩ የስንቅ አይነቶች ተዘጋጅቷል፣ 560 ኩንታል ወደ ግንባር ተልኳል፡፡ ቀሪው ከነገ ጀምሮ እንደሚላክ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ ሌሎች አካላትም የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
