የሕወሓትን ወንበዴና ሽፍታ ቡድን ለመደምሰስ ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡

135
የሕወሓትን ወንበዴና ሽፍታ ቡድን ለመደምሰስ ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ ህዳሴ ፓርቲ፣ ራያ ራዩማ ዴሞክራሲ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ነጻነት ፓርቲ በጋራ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
አሸባሪው ሕወሓት ቡድን የተለያዩ ሦስት ጦርነቶችን በማካሄድ የሦስት ትውልድ አጥንትና ደም ያፈሰሰ ጸረ ሰላምና አጥፊ ድርጅት ነው ብለዋል ፓርቲዎቹ በጋራ መግለጫቸው፡፡
ሕወሓት የጭቁን ሕዝቦች እፎይታና ሰላም የማይሻ እና ዘወትር በሰው ደም እየነገደ በስልጣን መቆየትን የሚፈልግ ድርጅት ነው ያለው የፓርቲዎቹ የጋራ መግለጫ በተለይ ደግሞ ሥራ ወዳድና ምስኪን በሆነው የትግራይ ሕዝብ ጉያ ውስጥ ተሸጉጦ ተራ ቃላት ሽንገላና የድረሱልኝ ጥሪ እያሰማ ታዳጊ ሕጻናት ሳይቀር ወደ ጦርነት ማግዷል፡፡ በዚህም የተነሳ ከአንድ የትግራይ ቤተሰብ ውስጥ ከ3 እስከ 4 ልጁንና ያልገበረ ቤተሰብ የለም፡፡ በዚህም ላይ የትግራይ ሕዝብ ከችግር ከእልቂት አንዳችም ያተረፈው ትርፍ የለም ብሏል፡፡
ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ እንደመሸሸጊያ ተጠቅሞ በአሁኑ ሰዓት መንግሥት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ መደኋላ በመተው በሦስት አቅጣጫ መጠነ ሰፊ ውጊያ መክፈቱንም ጠቅሷል፡፡
አሸባሪው ሕወሓት በከፈተው ውጊያ ሕጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያንን የሃይማኖት አባቶችን ከፊት ለፊት በማስቀደም የዓለም አቀፍ ሕግ የማይፈቅደውን ከ15 ዓመት በታች የሆኑትን ሕጻናትን በማሰለፍ በተለያዩ አደንዛዥ እጽ ሀሺሽ በመጠቀም ውጊያ እያካሄደ ይገኛል፡፡ በዚህም በአፋር ግንባር፣ በራያ ግንባርና በወልቃይት ግንባር በውጊያ ላይ ይገኛል ነው ያለው፡፡
ፓርቲዎቹ በጋራ መግለጫው እንዳሉት መንግሥት ያደረገው ጥሪ ድጋፍ ለመስጠትና የሕወሓትን ወንበዴና ሽፍታ ቡድን ለመደምሰስ ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን፡፡ የፓርቲ አባሎችም ኾነ አመራሮች ቦታው ድረስ በመሄድና በአውደ ውጊያ ግንባር በመዝመት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ወራሪውን የሕወሓት ርዝራዥ ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
“ሕወሓት ሕዝቡን እንደጋሻ መሸሸጊያ መጠቀሙ ምን ያህል ለራሱ ሕዝብ እንኳን ደንታ የሌለው መሆኑን የሚያሳይ የሚያስገነዝብ ጸረ ሕዝብና ጸረ ሀገር መሆኑን በግልጽ አሳይቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ጥሎብን የሄደው ጠባሳ ሳይሽር እንደገና ከጋሻ ጃግሬዎቹ ጋር በመሆን በላያችን ላይ ሊጭንብን ያሰበውን የጭቆናና የግፍ ቀንበር በተለይ ደግሞ በፕሮፖጋንዳው ሐሰት ዜና በማሰራጨት ሕዝቡን ውዥንብር ውስጥ በመክተት ከፍተኛ ስህተት እየሠራ ስለሆነ ከዚህ እኩይ ተግባሩ በመቆጠብ ታዳጊ ህጻናትን እና የሕዝብ ማዕበል ለጦርነት ከመጠቀም ተግባሩ ታቅቦ ከለላየ ነው ለሚለው ሕዝብ ህይወት መትረፍ ሊሠራ ይገባል እንላለን” ብሏል የፓርቲዎቹ መግለጫ፡፡
በየጊዜው የሚሰራጨውን የሕወሓት ወሬ ወደ ጎን በመተው ሕዝቡ ለሠራዊቱ ደጀን በመሆን አስፈላጊውን የሞራል፣ የስንቅና የተለያዩ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በመለገስ ደጀንነቱን በሁሉም መስክ አስተዋፅኦ እንዲያደርግም ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ ከአሸባሪ ቡድኑ ሕወሓት ተነጥሎ እንዲጓዝ እና አሸባሪው እርቃኑን እንዲቀር ያላሰለሰ ትግል እንዲያካሄድ ፤ ከወገኑ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ደጀን ኾኖ እንዲሰለፍ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ብለዋል፡፡
የጁንታው ቡድን የኢትዮጵያ ሕዝብ የተባበረ ክንድ የሚቀምስበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም መግለጫው መላው ሕዝብ ከትግራይ ወንድም እህት ከሆነው ሕዝብ ጋር በመታጋገዝና በመሰለፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሸባሪውና ጁንታውን የሕወሓት ቡድንን በአጭር ጊዜ መውጫና መግቢያ ብሎም መጠጊያ በማሳጣት እንደሚደመስስ አንጠራጠርም፡፡ ምንግዜም የተጨቆነ ሕዝብ ያሸንፋል ነው ብለዋል በጋራ መግለጫቸው፡፡
ሕዝብን ግራ የሚያጋቡ መረጃዎች እየተለቀቁ ስለሆነ መንግሥት የሕዝብ ግንኙነቱን አጠናክሮ ስለወቅታዊ ሁኔታዎች ለሚዲያም ኾነ ለሕዝብ ጠቃሚ ሐሳቦችን እንዲያካፍልም ፓርቲዎቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“በወልቃይት ጠገዴ በኩል መተላለፊያ ኮሪደር ይከፈት የሚለው ግፊት ተቀባይነት የለውም” አቶ ምትኩ ካሳ
Next articleየዓባይ ተፋሰስ ልማት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ አደረጉ።