የአማራ ፋኖ ሀገር አፍራሹን አሸባሪ ቡድን አከርካሪ ለመስበር ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከሁሉም ክልል ከተውጣጡ ልዩ ኅይሎችና ከአማራ ሚሊሻ ጋር በመኾን አኩሪ ድሎችን እያስመዘገበ ነው፡፡

1903

የአማራ ፋኖ ሀገር አፍራሹን አሸባሪ ቡድን አከርካሪ ለመስበር ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከሁሉም ክልል ከተውጣጡ ልዩ ኅይሎችና ከአማራ ሚሊሻ ጋር በመኾን አኩሪ ድሎችን እያስመዘገበ ነው፡፡

ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ፋኖ ሀገር አፍራሽ የአሸባሪውን አከርካሪ ለመስበር ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከሁሉም ክልል ከተውጣጡ ልዩ ኅይሎች፣ ከአማራ ሚሊሻና ከአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ጋር በመኾን ቅንጅታዋ ሥራ እያከናወነ አኩሪ ድሎችን እያስመዘገበ ነው፡፡

የአማራ ፋኖ ቀደም ብሎም የሀገረ ክብርና የሉዓላዊነት መገለጫ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በአሸባሪው ትህነግ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጥቃት ሲደርስበት የመንግሥትን ጥሪ በመቀበል በኢትዮጵያ ሕዝቦች ህልውና የመጣውን ጠላት ተፋልሟል።

የአማራ ፋኖ አርበኛ ገበየሁ እንየው ለጋዜጠኞች ቡድን እንደገለጸው ከምርጫ 97 በኋላ በዚሁ ቡድን ሲሳደዱ በዋሻ ውስጥ ቆይተዋል፤ የሉዓላዊነት መገለጫ በኾነው በሀገር መከላከያ ሠራዊት ጥቃት ሲፈጸም ለአሸባሪው ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኀይልና ከአማራ ሚሊሻ ጎን በመሰለፍ የአጸፋ መልስ ሰጥቷል፤ ዛሬም አኩሪ ድል እየፈጸሙ ነው።

ፋኖ አካባቢውን ጠንቅቆ የሚያውቅ በመኾኑ በተሠለፈባቸው አውደ ውጊያዎች ሁሉ ብዙ ምሽጎችን ሰብሮ መግባቱንም አርበኛ ገበየሁ ተናግሯል። በአሁኑ ወቅትም አሸባሪው በተከዜ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎችን ለቆ እንዲወጣ ከወገን ጦር ጋር በመኾን ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውን አስረድቷል።

ጁንታው በደረሠባቸው አካባቢዎች ሁሉ በሕፃናት፣ በእናቶች፣ በአዛውንቶች፣ በሃይማኖት አባቶች እና በኅብረተሰቡ እያደረሰ ያለውን በደል መመለስ የሚቻለውም የጁንታውን አከርካሪ በመስበር ነው ብሏል አርበኛ ገበየሁ። ለዚህም የአማራ ፋኖ ከወገን ጦር ጋር በመኾን በጠንካራ አደረጃጀት እየታገለ ነው ብሏል።

አሸባሪው ቡድን ፊት ለፊት ለመግጠም ምንም አቅሙና ዝግጁነት እንደሌለው አስረድቷል። እንደማሳያ ከሰሞኑ የአሸባሪው ቡድን አባላት በአዲአርቃይ ወረዳ ወቅታዊ ዝናብና ጉምን ሽፋን አድርገው ሰርገው ሲገቡ በማገኘት ታላቅ ጀብዱ እንደፈጸሙ ነግሮናል፡፡

አሸባሪው ቡድን ሕዝብን ሊያተራምስ ከሰይጣን የተላከ ውላጅ ነው ያለው የአማራ ፋኖ ገበየሁ አመጣጡም የሠው ነፍስ እየበላ ነው ብሏል። በመሆኑም በጠንካራ ሥነ ልቦና እና አደረጃጀት ውስጥ ኾነው ጠላትን እያሽመደመዱ መምጣታቸውን ተናግሯል። አሁንም አላርፍ ብሎ ሕዝብ እየበላ ስለመጣ የጁንታውን አከርካሪ ለመምታት ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጧል።

በሁሉም ጫፍ ያሉ ዜጎችም ጉዳዩ ሀገር የማፍረስ እንደኾነ በመገንዘብ ጁንታውን ለመደምስስ በተደረገው የክተት ጥሪ የሚጠበቅባቸውን ማበርከት እንደሚገባቸው ተናግሯል። አሸባሪው ቡድን ከዚህ በፊት የኢትዮጵያን መሣሪያና ገንዘብ ይዞ አቅም እንደሌለው በሶስት ሳምንት ዘመቻ ታይቷል ብሏል።

ያም ኾኖ ተልዕኮን በአጭር ቀናት ለመጨረስ ሰው በአለው አቅሙ መደገፍ አለበት ብሏል። አሸባሪው ለ27 ዓመታት የተካነውን የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመጠቀም በእውነትና በእምነት በሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሀሰት ወሬ እያሠራጨ ነው፤ ሰው አሁንም መንቃት አለበት፤ ይልቁንም ገንዘብ ያለው በገንዘብ፣ ሌላውም በሚችለው ልክ አንድ ላይ በመኾን ለኢትዮጵያ የተረጨውን መርዝ ማጥፋት ይገባል ነው ያለው።

ዘጋቢ:-አዳሙ ሽባባው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየታጋይ መብራቱ የትግል ጉዞ ከፍል ሁለት
Next articleበእነ ዶክተር ደብረፅዮን የክስ መዝገብ ከተከሰሱ 62 ተከሳሾች መካከል 19ኙ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ በጽሑፍ እንዲደርሳቸው ተደረገ፡፡