
የታጋይ መብራቱ የትግል ጉዞ ከፍል ሁለት
ባሕር ዳር: ሐምሌ 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ታጋይ መብራቱ ከከፋኝ ምስረታ እስከ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባልነት ሲንቀሳቀሱ በትህነግ በኩል ከፍተኛ ክትትል ቢደረግባቸውም በብልሃትና በድፍረት ተጋፍጠው አልፈዋል። ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳያቸውን ጨርሰው ጎንደር ላይ ሥራቸውን እያከናወኑ ባለበት ጊዜ ግን የትግል አጋሮቻቸው ታፈኑ። እርሳቸውን ለማፈንም ተደጋጋሚ ሙከራ ተደረገ። በተለይ ቃብትያ ላይ ለማፈን ከተከበቡ በኋላ ሰብረው መውጣት የቻሉ ቆራጥ ታጋይ ናቸው።
አርበኛ መብራቱ ትህነግ ኮቴያቸውን እየተከተለ ቢያሳድዳቸውም ሸብረክ ሳይሉ የትግላቸውን መጨረሻ ለማየት በድፍረት ቀጥለዋል።
ታዲያ ሀገር አማን ብለው ጎንደር ላይ ሐምሌ 5/2008 ዓ.ም ጥዋት መድኃኔዓለም ቤተ- ክርስቲያን እየተሳለሙ ሳለ ትህነግ ወደ ጎንደር ባሰማራቸው የደኅንነት ሰዎች ታፍነው ተወሰዱ። በዚያ ዕለት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ጨምሮ ሌሎች የኮሚቴ አባላትን ካሉበት ለማፈን እንቅስቃሴ ተደርጓል።
ታጋይ መብራቱ ተይዘው ከገቡ በኋላ ወደ ማዕከላዊ ተወስደዋል። ማዕከላዊም ቢኾን ተባይ የፈላበት፣ ምንም ሰው የሌለበት፣ መቆሚያ መቀመጫ የሌለው፣ ጨለማና ስቃይ በበዛበት ክፍል ነው የታሰሩት። ምርመራ የሚደረገው ደግሞ ከሌሊቱ 4:00 ጀምሮ እስከ 9:00 ባለው ጊዜ ነው። እስር ቤት እያሉ ድብደባ ይደርስባቸው ስለነበር አንድም ለማምለጥ አለበለዚያም ገጥሞ ለመሞት ይወስኑና እስር ቤት መሣሪያ ለማስገባት ሞክረው ከሸፈባቸው። ድብደባ በደረሰባቸው ጊዜ አይናቸውን ስለተመቱ ደም ፈስሷቸው ነበር።
ማዕከላዊ በገቡ በአራት ወራቸው የተሻለ ቦታ እንዲዛወሩ ከተደረገ በኋላ በአሸባሪነት ተፈርጀው 156 ገጽ ያለው ክስ ተመሰረተባቸው። ለፍርድ የተቀመጠው የትህነግ ሰው ነበርና ጉዳዬ በሌላ ዳኛ ይታይልኝ በማለታቸው ችሎት ደፍረዋል በሚል ሰበብ የአምስት ወር እስራት እንደተፈረደባቸው አስታውሰዋል።
ከዚያም የለውጡ አስተዳደርም በሕግ አግባብ ለቀረበ የሕዝብ ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ መስጠት እንጂ ሰው መሰቃየት የለበትም በሚል እንዲለቀቁ ኾኗል። ማዕከላዊ እያሉ ዓይናቸውን በመመታታቸው ከውጪ ሀገር መነጽር እንዲመጣላቸው ተደረገ። ወደፊት ገና ብዙ ትግል ስለሚጠብቃቸው ተኩስ እንዳይከለክላቸው ክፉኛ ሰግተው ነበር። ነገር ግን ዒላማ ሞክረው ስኬታማ በመኾናቸው ደስታቸው ወደር አልነበረውም። ከእስር እንደተፈቱም ጀግና ወዳዱ፣ ውለታ አክባሪውና ታሪክ ሠሪው የጎንደር ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የጀግና አቀባበል አደረገላቸው። አሁንም በስስት እንደ ዓይኑ ብሌን እየተንከባከባቸው ይገኛል።
እሳቸውም ከሌሎች የትግል አጋሮቻቸው ጋር በመኾን ትግላቸውን ቀጥለዋል። የሚደረግባቸው ክትትል ስለተጠናከረ ከወልቃይት ውጪ ኾነው ጉዳዩን እንዲያስፈጽሙ ተደረገ። ኮሚቴው ሕጋዊ አካሄድ ቢከተልም ትህነግ በሕገወጥ መልኩ ማሳደዱን አላቆመም። ከዚያም በጎንደር መላ ሕዝቡን በተለይም ወጣቱን የማደራጀት ሥራ ሠርተዋል። በማይደሌ፣ ግጨው፣ ጠገዴና ቃብትያ የሽምቅ ውጊያ በመክፈትም የትህነግን ቡድን ድጋሜ ሽንፈት አከናንበዋል።
በዚያ መሀል ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም አሸባሪው የትህነግ ቡድን የማይደፈረውን ደፍሮ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ባጠቃ ጊዜ አርበኞች ፈጥነው ሥራቸውን ጀመሩ። በሌሊቱ ከሻለቃ ደጀኔ ማሩ ጋር በመደዋወል ሠራዊታቸውን አንቀሳቅሰው ግማሹ በሶሮቃ እሳቸው የሚመሩት ኀይል ደግሞ በቅራቅር በኩል ትቢት የወጠረውን ኀይል ያስተነፍሱት ጀመሩ። በሶስት መኪና ወደ ሥፍራው ያቀናን የጠላት ኀይል ለወሬ ነጋሪ እንኳን እንዳይተርፍ አድርገው ደመሰሱ። ስድስት ቀን ይወስዳል የተባለውን ጦርነት ከአንድ ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ በስኬት ፈጸሙት። የሚማረከውን ማርከው፣ የሚደመሰሰውንም ደምስሰው አካባቢውን እያጸዱ ወደፊት መገስገሳቸውን ቀጠሉ።
በርካታ አካባቢዎችን እያካለሉ የወልቃይትን ሕዝብ የዘመናት ጨለማ በብርሃን እየተኩ ገሰገሱ። አርብ ገበያን ነጻ አውጥተው ደጀና ላይ ተሰለፉ። ከመከላከያና ከአማራ ልዩ ኀይል ጋር እየመከሩ የጠላትን ምሽግ ደርምሰው ወፍ አርግፍ ከተማን ተቆጣጠሩ። የወፍ አርግፍ ከተማ ሕዝብም የሚበላና የሚጠጣ አዘጋጅቶ ሰንደቅ ዓላማውን እያውለበለበ ጀግኖቹን በደስታ ተቀበለ። በሬ አርዶም ጋበዘ። በዚያን ጊዜ በታጋዩና በሕዝቡ መካከል ልዩ ደስታ ተፈጠረ።
የዓመታት የጭቆና ቀንበር ተሰብሮ ንጹኃን ነጻ ወጡ፣ ታጋዮችም የልፋታቸውን ዋጋ አግኝተዋልና በደስታ እንባ ተራጩ። አርበኞቹ ጊዜ ሳያጠፉ ወደ ተከዜ ገሰገሱ። ማይጋባ ላይ ለአራት ሰዓት የፈጀ ውጊያ በማድረግ የአሸባሪውን ቡድን ምሽግ ሰብረው ጠላትን ደመሰሱ። ከዚያም እሳቸው የሚመሩት ሠራዊት ወደ ሁመራ፣ ወፍ አርግፍ፣ ዳንሻ፣ ወይ እናት በርሃ እና ሌሎች አካባቢዎች ተከፋፍለው አካባቢን የመጠበቅ ስምሪት ወስደዋል።
አርበኛ መብራቱ አሁን የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ እያደራጁ ይገኛሉ። በአሸባሪው ትህነግ እልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና በደል ተሰድደው የነበሩ ሰዎችም ወደ ቀደመ ርስታቸው እየተመለሱ ነው። ሕዝብ፣ መንግሥትና አርበኞች እጅና ጓንት ኾነው አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ ይገኛሉ። ጥሩ የመረጃ ቅብብሎሽም አለ። የአካባቢውን ሰላም ለመረበሽ የሚያስብ ግን ፈጽሞ አይሳካለትም፣ ምክንያቱም የወልቃይት ሕዝብና አርበኞች የክንዳቸው ወላፈን በሩቁ አቃጥሎ ይመልሳል እንጂ አያስጠጋም።
የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያውያን ጋር ኾኖ ታሪክ መሥራት ያውቅበታል። በተደጋጋሚ በሀገርና በሕዝብ ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን መክቶ ሀገር በማቆየትም አኩሪ ገድል ፈጽሟል። የእነ አርበኛ መብራቱ የዓመታት ተጋድሎ የትህነግን ውስብስብ ሴራ ገዝግዞ ኢትዮጵያን ታድጓል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
