
የቀድሞ የኢትዮጵያ የአየር ወለድ ሠራዊት አባላት አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን ለመደምሰስ መንግሥት የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ።
ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ወለድ ሠራዊት ማኅበር ዛሬ በቢሾፍቱ ባካሄደው መርኃ ግብር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም ገልጿል።
የማኅበሩ የበላይ ጠባቂ ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ ሃብተማርያም እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከውስጥም ከውጭም ጦርነት ታውጆባታል። ይህንንም ተከትሎ ቀድሞ የሠራዊቱ አባላት ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር ለመመከትና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የአቅማቸውን ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ከቀድሞ ሠራዊቱ አባላት መካከል አቅም ያላቸው ወደ ግንባር ለመዝመት መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል፡፡ አቅም የሌላቸው ደግሞ አስፈላጊውን ሙያዊ ሥልጠና ለመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ቀሪው ደግሞ መንግሥት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ አስተዋጽዖ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የቀድሞ ሠራዊት ለኢትዮጵያ አንድነት ትልቅ መስዋእትነት መክፈሉን ገልጸው፤ አሁንም “ሀገር ሲፈርስ ቁጭ ብሎ ማየት አይችልም” ብለዋል።
አሸባሪው ሕወሓት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በጥቅም ለመሸጥ እየሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ሕዝቡም ይህንን እኩይ ተግባር ለመመከት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አድንቀዋል።
የማኅበሩ ምክትል የበላይ ጠባቂ ኮሎኔል ታምሩ ኃይሉ በበኩላቸው፤ የቀድሞ ሠራዊት በአውደ ውጊያ የራሱ የኾነ ክህሎትና ብቃት ያለው መሆኑን አስታውሰዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩ በርካታ ጥቃቶችን በመመከት ብርቱ ክንድ ማሳየቱን ገልጸው፤ አሁንም ይህንን ጀግንቱን እንደሚደግመው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
