“አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታራምደውን የተሳሳተ አካሄድ ለማረም አልረፈደባትም” ላውረንስ ፍሪማን

385
“አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታራምደውን የተሳሳተ አካሄድ ለማረም አልረፈደባትም” ላውረንስ ፍሪማን
ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አፍሪካን በሚመለከቱ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተንታኝ፣ ጸሐፊ እና ተመራማሪ ናቸው ላውረንስ ፍሪማን፡፡ በሰሞኑ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊ ትንታኔያቸው ከ120 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረውን እና በአሜሪካ መንግሥት የተዛባ እይታ ምክንያት እክል የገጠመውን የኢትዮ-አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዳስሰዋል፡፡ አሜሪካ በአፍሪካ በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ እያራመደችው ያለውን ፖሊሲ እንድትፈትሽ የምትገደድበት ወቅት ላይ ናት ይላሉ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የቀጣናውን ጉዳይ የተካኑት ላውረንስ ፍሪማን፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛዋ ሀገር ናት፤ 110 ሚሊየን የሚጠጋውን ሕዝቧን ከድህነት ለማውጣት ተስፋ ሰጭ የልማት ፕሮጀክቶችን ቀይሳለች የሚሉት ፍሪማን ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ሁለት ስኬታማ ተግባራትን ፈጽማለች ይላሉ ፤ ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ እና የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በማንሳት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በስልጣን በቆዩበት ያለፉት ስድስት ወራት አፍሪካን በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያን በሚመለከት ያራመዱት ፖሊሲ ጤነኛ አልነበረም ነው ያሉት፡፡
ከአፍሪካ አህጉር ባልተለመደ መልኩ ኢትዮጵያ ያካሄደችው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ኾኖ ሳለ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለዚህ አፈፃጸም እውቅና መስጠት የፈለጉ አይመስሉም ያሉት ተንታኙ እናወዳድር ቢባል እንኳን እርሳቸው ወደስልጣን የመጡበት የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ምን ያክል ግጭት እና ብጥብጥ ማስነሳቱን መዘንጋት አይገባም ይላሉ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ 14 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የያዘውን የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ፕሬዚዳንት ባይደን እና ዲሞክራቶቹ የሚመሩት የአሜሪካ ኮንግረንስ ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የተለየ አልነበረም ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ይላሉ እውቁ የአፍሪካ ቀንድ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለአፍሪካ አህጉር ተስፋ ሰጭ የልማት እና የእድገት ጥረቶችን እያሳየችው ላለችው ኢትዮጵያ እና ለለውጡ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እውቅና መስጠት የፈለጉ አይመስሉም ነው ያሉት፡፡
አሜሪካ ስለዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት እና የሕግ የበላይነት ጥብቅና እቆማለሁ የምትል ሀገር ኾና ሳለ የራስን ፍላጎት በሌሎች ሀገሮች ላይ ከመጫን የበለጠ ምን ጥሰት አለ? የሚሉት ላውረንስ ፍሪማን “አሜሪካ በአፍሪካ አህጉር በተለይም በኢትዮጵያ ላይ የምታራምደው ፖሊሲ ሚዛኑን ስቷል” ነው ያሉት፡፡
የአሜሪካ መንግሥት ከአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ጋር ድርድር እንዲካሄድ እየጠበቀ ይሆን? ሲሉ የጠየቁት ላውረንስ ፍሪማን አሸባሪው ቡድን በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች እየፈጸመው ላለው ሽብር እና ጦር የልብ ልብ የሰጠው የአሜሪካ መንግሥት ኀላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው፤ በእርግጥስ ለሚደርሰው ሰብዓዊ ጥፋት ኀላፊነቱን ይወስዳል? ሲሉም ያነሳሉ፡፡
የሊቢያን ጉዳይ ዋቢ ያደረጉት ላውረንስ ፍሪማን ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ግጭት ተነስቶ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ እጣ ፋንታ ቢገጥማት ጉዳቱ የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ለከፋ አደጋ ይጋለጣሉ ነው ያሉት።
በመጨረሻም ተንታኙ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታራምደውን የተሳሳተ አካሄድ ለማረም አልረፈደባትም ይላሉ በምክረ ሐሳባቸው፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article”ከአባቶቻችን በወረስነው ወኔና ጀግንነት፣ አሸባሪው ትህነግን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ደምስሰን ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ሁላችንም እንዝመት” የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ወንዴ መሰረት
Next articleለክቡር ዶክተር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እና ለቀድሞው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ በስማቸው ጎዳና የመሰየም ሥነ ሥርዓት በጎንደር ከተማ ተካሄደ።