
”ከአባቶቻችን በወረስነው ወኔና ጀግንነት፣ አሸባሪው ትህነግን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ደምስሰን ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ሁላችንም እንዝመት” የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ወንዴ መሰረት
ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረታቦር ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያን ለመበታተን የከፈተውን ጦርነት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ በተለያዩ አቅጣጫዎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የጦር ነጋሪት ጉሰማውን ቀጥሎበታል፡፡ ያለፈው ጥፋትና በደሉ አልበቃው ብሎ ኢትዮጵያን ለመበታተን የተነሳውን አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ኢትጵያውያን እየተረባረቡ ይገኛል፡፡
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ ወንዴ መሰረት ኢትዮጵያን የማፈራረስ ህልም ያለው አሸባሪው ትህነግ ጦርነት ከፍቷል ብለዋል፡፡

አሸባሪው ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን ግፍና በደል የዓለም ማኅበረሰብ እንዳላየ እያለፈው ነው ያሉት ከንቲባው ሕጻናትንና አዛውንትን ለጦርነት በማሰለፍ አቅሙን አሟጦ እየተረባረበ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአሸባሪውን ትህነግ አፍራሽ ተልዕኮ የመመከትና የመደምሰስ ሥራ እየተሠራ መሆኑንና ለዚሁ ዓላማም የአማራ ክልል የክተት ጥሪ ማድረጉን አቶ ወንዴ አስታውሰዋል፡፡
አቶ ወንዴ ”ከአባቶቻችን በወረስነው ወኔና ጀግንነት፣ አሸባሪው ትህነግን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ደምስሰን ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ሁላችንም እንዝመት”ብለዋል፡፡
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተገኙ ነዋሪዎች አሸባሪውን ትህነግ በመደምሰስ ኢትዮጵያ የተደቀነባትን ሰንኮፍ እንደሚነቅሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለማዳን እንዘምታለን፣ ሰልጥን፣ ታጠቅ፣ ለሀገርህ ህልውና ዘብ ቁም፣ ጁንታውን ከምድር እናጠፋለን የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች በሰልፉ ላይ ተስተጋብተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ – ከደብረታቦር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
