
በበይነ መረብና በሞባይል ባንኪንግ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር: ሐምሌ 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ ኅብረተሰቡ በስጦታ፣ በቦንድ ግዢ፣ በ8100Aና በመሳሰሉት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ አሁንም በተጨማሪ የሀብት ማሰባሰቡ ሂደት በበይነ መረብ እና በሞባይል ባንኪንግ አማካኝነት ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለአሚኮ ተናግረዋል።
“www.mygerd.com” የተሰኘው ድረ ገጽ በይፋ ከተከፈተ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ100 ሺህ ዶላር በላይ ሀብት ማሰባሰብ እንደተቻለ አቶ ኃይሉ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ኅብረተሰቡ የቴሌ ብር መተግበሪያን በመጠቀም ለግድቡ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ 30 ሺህ ብር ገቢ መሰብሰቡን አስረድተዋል፡፡ ይህን ሀብት ማሰባሰብ የተቻለው ከጅምሩ መተግበሪያው በሚተዋወቅበት ወቅት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
