
ባሕር ዳር፡ መስከረም 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) በኳታር አስተናጋጅነት የፊታችን ዓርብ መስከረም 16/2012 ዓ.ም 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና ይጀመራል፤ በዚህ ውድድር የሚሳተፉ የስፖርት ልዑካን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ልዑክ ኳታር ዶሃ መግባቱ ነው የተገለጸው።
የአትሌቲክስ ልዑኩ ከሌሊቱ 8፡00 ላይ በዶሃ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ እና በኳታር የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሳሚያ ዘካርያ አቀባበል አድርገውለታል።
ኢትዮጵያ በሻምፕዮናው በመካከለኛ፣ በረጅም ርቀት እና በሀገር አቋራጭ የሩጫ ውድድሮች ትሳተፋለች። በወጣው የውድድር መርሀ ግብር መሠረት ከዓርብ መስከረም 16/2012 ዓ.ም ጀምሮ አትሌቶች የማጣሪያ እና የፍጻሜ ውድድራቸውን ያደርጋሉ።
በሴቶች ማራቶን አትሌት ሮዛ ደረጀ፣ ሩቲ አጋ እና ሹሬ ደምሴ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ፡፡ ዓርብ ምሽት 1፡00 ላይ በ 3 ሺህ ሜትር ማጣሪያ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉት አትሌቶች መቅደስ አበበ፣ ዘርፌ ልመንህ እና ሎሚ ሙለታ ናቸው፡፡ በ800 ሜትር ደግሞ አትሌት ደርቤ ወልተጂ በማጣሪያ ውድድር ትሳተፋለች።
ዓርብ ምሽት በሚደረግ የወንዶች 5 ሺህ ሜትር የማጣሪያ ውድድር ላይ አትሌት ሙክታር ኢድሪስ፣ ጥላሁን ኃይሌ፣ ሰለሞን ባረጋ እና አባዲ ሓዲስ ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን
በደጀኔ በቀለ