
እየተደረገ ባለው የህልውናና የፍትሕ ጦርነት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።
ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ ባለሃብቶች፣ ታዋቂ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ወጣቶች እና የወጣት ተወካዮች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ወኪሎች የተሳተፉበት የአማራ ጉባኤ ተካሂዷል።
የአማራ ጉባኤ ያሳለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመድረኩ ስለ ጦርነቱ እና በቀጣይ መደረግ ስለሚገባቸው ጉዳዮች የተመለከተ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት መደረጉን አቶ ግዛቸው ገልጸዋል።
በቀጣይ እነዚህ የኅብረሰተሰብ ወኪሎች በህልውና ዘመቻው በሙሉ አቅማቸው ለመደገፍ እና ለመሳተፍ መወሰናቸውን አብራርተዋል።
አቶ ግዛቸው አሸባሪው ትህነግ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ እያደረገ ያለው ጦርነት በውጭ ኀይሎች የሚደገፍ እንደኾነ አንስተዋል።
አሸባሪው ትህነግ በሀገሪቱ በሰብዓዊ እና ቁሳዊ ሀብቶች ላይ ጉዳት ያደረሰ ቡድን እንደኾነም በመግለጫው አመላክተዋል።
አቶ ግዛቸው እንዳሉት አሸባሪው ትህነግ የሀገር አለኝታ የኾነውን የሀገር የመከላከያ ሠራዊት በመውጋት የጀመረውን ጥፋት አሁንም ከውጭ ጠላቶች ጋር በመኾን መንግሥት ያደረገውን የተናጠል የተኩስ አቁም ጥሶ ዳግም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው።
ትህነግ ከመነሻው ጀምሮ የአማራን ሕዝብ በጠላትነት በመፈረጅ በጅምላ ሲረሽን መቆየቱን ያነሱት አቶ ግዛቸው በዚህ ወቅትም በአማራ ላይ ጦርነት በመክፈት ጉዳት ማድረሱን አንስተዋል። ቡድኑ የሚያዋጋው ኀይል በመደምሰሱ ሕፃናትን፣ ሴቶችን እና አርሶ አደሮችን በማስገደድ እየማገደ እንደኾነም ጠቅሰዋል።
አቶ ግዛቸው ጦርነቱ በአማራ ላይ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ላይ ጭምር የተከፈተ በመኾኑ መላው ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። ይህም በአፋር ላይ የተደረገው ወረራ አንዱ ማሳያ እንደኾነ አንስተዋል።
ወጣቶች ለህልውና ትግሉ የሚቆሙበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን መኾኑን አውቀው እየተከናወነ በሚገኘው የሀገር መከላከያ፣ የልዩ ኀይል እና የሚሊሻ ምልመላ በሚፈልጉት አማራጭ በመቀላቀል ትግሉን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
በተለይም የመከላከያ ሠራዊቱን ተዋጽኦ ለማስጠበቅ ወጣቶች ተቋሙን እንዲቀላቀሉ አሳስበዋል።
ምሁራንም ወደ ቀያቸው በመሄድ ማኅበረሰቡን የማንቃት ሥራ መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የሃይማኖት አባቶች ትህነግ ባለፉት ዓመታት የሃይማኖት ግብረገብን በመሸርሸር ጥፋት ሲያደርስ የኖረ ቡድን መኾኑን ተገንዝበው ለዳግም ጭቆና የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በየ ቤተ እምነቱ ሊያወግዙ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
