‹‹አጋጣሚው ከሥራ ዕድል ፈጠራ በዘለለ የወሎን ሕዝብ ከፍታ ለአምባሳደሮቻችን የምናሳይበት መልካም ዕድል በመሆኑ በቂ ዝግጅት አድርገናል፡፡›› የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ

249

ባሕር ዳር፡ መስከረም 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) ግሸን ደብረ ከርቤ ማሪያም በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ከደሴ ከተማ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በ82 ኪሎ ሜትር ርቀት ከፍ ብላ አምባው ላይ ትገኛለች፡፡

ግሸን ደብረ ከርቤ ማሪያም በ517 ዓ.ም አባ ፈቃደ ክርስቶስ በተባሉ የሃይማኖት አባት እንደተመሠረተች ይነገራል፡፡ ከ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ደግሞ ግሸን ከእምነት ስፍራነቷ በተጨማሪ የነገሥታት ልጆች መቀመጫ ሆናም አገልግላ ነበር፡፡ የአሁኑን ክብሯን እና ዝናዋን ያገኘችበት ምክንያት የተፈጠረው ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል በቦታው የሚገኝ መሆኑ ነው፡፡ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ በነገሡ ዘመን መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም ግማደ መስቀሉን ይዘው ግሸን በመድረስ፣ ከአራት ዓመታት በኋላ መስከረም 21 ቀን 1449 ዓ.ም ጀምሮ የንግሥ በዓሏ መከበር እንደጀመረ ይነገራል፡፡

በየዓመቱ መስከረም 21 ቀን የንግሥ በዓሏን ለማክበር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመኖቿ ከመላው ዓለም ይሰባሰባሉ፡፡ በዚህ መልክ የሚከበረው የግሸን ደብረ ከርቤ የዘንድሮውን 563ኛ ዓመት የንግሥ በዓል ለማክበር ከ3 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ ሙሐመድ በተለይም ለአብመድ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል፡፡

‹‹ከዘንድሮውን የግሸን ደብረ ከርቤ የንግሥ በዓል ጋር ተያይዞ ሌሎች ተከታታይ ሁነቶችም ከበዓሉ በፊት ይኖራሉ›› ያሉት አቶ ሰይድ የመስቀል በዓል እና በአማራ ክልል ለ27ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለም የቱሪዝም ቀን በግሸን እንደሚከበሩም ተናግረዋል፡፡ በግሸን ደብረ ከርቤ ማሪያም አምባ ላይ የተገነባው የባሕል ሙዚዬምም በዚሁ ወቅት እንደሚመረቅ አቶ ሰይድ ገልፀዋል፡፡

‹‹ወደ ግሸን የሚመጡ እንግዶች የትራንስፖርት ችግር እንዳይገጥማቸው በሁለት አቅጣጫ የመንገድ ጥገና ተደርጓል፡፡ ከደሴ-ኩታ በር-ተለያየን እስከ ግሸን እና ከሐይቅ እና ውጫሌ- ጨፌ እስከ ግሸን ያሉት መንገዶች ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል›› ተብሏል፡፡ የውኃ እጥረት እና የጤና ችግር እንዳይፈጠር ወደ አካባቢው የጤና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መሠማራታቸውን ምክትል አስተዳዳሪው ነግረውናል፡፡

ከመስከረም 10 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ምዕመናኑ ወደ ስፍራው እየሄዱ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰይድ እንግዶች ስጋት እንዳይገባቸው በቂ የፀጥታ ኃይል ተዘጋጅቷል ብለውናል፡፡

በዘንድሮው የግሸን ደብረ ከርቤ የንግሥ በዓል ላይ ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ ነው፡፡ ‹‹ከቱሪስቶች ከሚገኘው ገቢ በላይ ይህን አጋጣሚ ከሥራ ዕድል ፈጠራ በዘለለ የወሎን ሕዝብ ከፍታ ለአምባሳደሮቻችን የምናሳይበት መልካም ዕድል በመሆኑ በቂ ዝግጅት አድርገናል›› ብለዋል ምክትል አስተዳዳሪው፡፡

አቶ ሰይድ በመልዕክታቸው በግሸን አምባ አካባቢ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችን እና ሎጅዎችን በመገንባት አካባቢውን ለቱሪስት ምቹ ለማድረግ እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ድጋፍ እንዲያደርጉ ለባለሀብቶች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Previous articleበሀገሪቱ የቫይረሱ ስርጭት 4 ነጥብ 9 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡
Next articleበ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የመጀመሪያው ልዑክ ዶሃ ገብቷል፡፡