“ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለዓመታት የጣሩ ሁሉ እንደማይሳካላቸው ኢትዮጵያዊያን በተግባር አሳይተዋል፤ ወደፊትም አንድነቷን ጠብቃ ጠላቶቿን ድል ታደርጋለች” ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ

148

“ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለዓመታት የጣሩ ሁሉ እንደማይሳካላቸው ኢትዮጵያዊያን በተግባር አሳይተዋል፤ ወደፊትም አንድነቷን ጠብቃ ጠላቶቿን ድል ታደርጋለች” ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የውኃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በብዙ ልፋት እና ጥረት ለምረቃ ለበቁ ተማሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በሕዝብ የጋራ ትብብር እና ጥረት እየተገነባ ያለውን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለማስቆም የተሸረበውን ሴራ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኩል ለማስቆም የተደረገው ጥረት ኢትዮጵያ በያዘችው እውነት ሴራውን በማምከን ጠላቶቿን ድል ያደረገችበት ጊዜ ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በራሷ ቁማ ያሰበችውን ማሳካት እንደምትችል ያሳየችበት፤ የታችኛው የተፋሰስ ሀገራት የሚፈጥሩባትን ሴራ ማምከን እንደምትችል ያረጋገጠችበት፤የሕዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት የተጠናቀቀበት፤ ከውኃ ሙሌቱ ባሻገርም ኃይል ለማመንጨት የተዘጋጀንበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡

ሀገሪቷ ላይ በቅለው ከጠላቶቿ ጋር ቆመው አንድ እንዳንኾን በልዩነቶች ላይ ለዓመታት ያሴሩት ሴራ በሀገራቸው በማይደራደሩ ልጆቿ መምከን መቻሉን ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ተናግረዋል።

በአድዋ የታየው የኢትዮጵያ ልጆች ጽናት በሕዳሴው ግድብም መደገሙን የተናገሩት ሚኒስትሩ ይህም ወዳጆቿን ብቻ ሳይሆን ጠላቶቿንም አስደምሟል ነው ያሉት፡፡

በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ምክንያት በአንድ አይቆሙም ይፈርሳሉ ብለው ያሰቡትን ሴራ ኢትዮጵያዊያን ሰላማዊ ምርጫ በማካሄድ ጠላቶቿን አንገት አስደፍተዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በብዙ ስኬቶች ብታልፍም ብዙ ችግሮችንም ማለፏን ተናግረዋል፤ እንደ አንበጣ መንጋ፤ የጎርፍ አደጋና የእንቦጭ አረም የተከሰቱ ችግሮች ሲኾኑ ይህንንም በተባበረ ክንድ መፍታት እንደሚቻል የታየበት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ሀገሪቱ በዚህ ዓመት እስከ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እየተንቀሳቀሰች እንደኾነ ያብራሩት ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ወደ ጎረቤት የተፋሰሱ ሀገራት እስከ 1 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የማጓጓዝ ሥራ እየከወነች እንደኾነም አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል እና ወደ ውጭ ለመላክ የበጋ የመስኖ ስንዴን ለማምረት ያደረገችው ጥረት አበረታች ውጤት እንዳመጣም አንስተዋል። ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ኢትዮጵያን ለመበተን ለዓመታት የጣሩ ቡድኖች ሁሉ እንደማይሳካላቸው ኢትዮጵያዊያን በተግባር አሳይተዋል፤ ወደፊትም አንድነቷን ጠብቃ ጠላቶቿን ድል ታደርጋለች ነው ያሉት፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለማኀበረሰቡ የሚሠራው ተግባራዊ ሥራ እውቅና የሚሰጠው እንደኾነ የተናገሩት ሚኒስትሩ ተመራቂ ተማሪዎች በቀሰሙት እውቀት የተግባር ሥራ በመሥራት ትልቅ የነበረችውን ሀገራቸውን ወደ ማማው እንድትወጣ የበኩላቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምስጋናው ብርሃኔ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በልዩ ልዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።
Next article‹‹እናት ከመጨረሻው ምጥ በኋላ አዲስ ልጇን አይታ እንደምትደሰተው ሁሉ ኢትዮጵያም ከገጠማት ከባድ አደጋ በድል ወጥታ ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ ይሆናል›› አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን