
ʺአንበሳውን ነኩት እነ ልክ አያውቁ
ምን እንደሚያመጣ ቀድመው ሳይጠይቁ”
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 24/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ፈሪዎች በስሙ ይሸበራሉ፣ በግርማው ይደነግጣሉ፣ በአሻጋር ሲያዩት ይደነብራሉ፣ ጀግኖች በጀግንነቱ ይደነቃሉ፣ መንገዱን ይከተላሉ፣ በግርማው ይኮራሉ፣ በስሙ ይጠራሉ፣ በጥበቡ ይጓዛሉ፣ በዝናው ይደሰታሉ፡፡ ገፉት ጣላቸው፣ ገጠሙት መታቸው፣ ሞገቱት ረታቸው፣ ከክብር ውረድ አሉት በብዙ እጥፍ ልቆ ከፍ ብሎ ታያቸው፡፡ ቸኩሎ አይጣላም፣ ከሰው መርጦ አይጠላም፣ ምን ጭንቅ ቢሆን አይፈራም፣ ካልነኩት አይነካም፣ ስለ ፍቅር ይሞታል፣ ስለ ክብር ይዘምታል፣ አደባልቆ ያርሳል፣ አነጣጥሮ ይተኩሳል፣ በጀግንነቱ ለተከፋ ይደርሳል፣ ክብር ያስመልሳል፣ ጠላትን በአሻገር ይመልሳል፣ ጀብደኝነቱ አንጄት ያርሳል፣ ትህትናው ያሳሳል፣ ለጋስነቱ አንጄት ያላውሳል፣ አፈር ልሁን እያለ ያጎርሳል፣ ኩሎ ይድራል፣ ከአልጋ ወርዶ እንግዳ ያሳድራል፡፡
ፈጣሪውን የሚፈራ፣ ለተቸገሩት የሚራራ፣ በምድር ጥበብና ፍቅር የሚዘራ፣ ድንጋይ እንደ እንጨት የሚቀርጽ፣ ከዓለም በተቃራኒ ከላይ ወደታች የሚያንፅ፣ በዘመኑ ታሪክ ሠሪ፣ ለለተኪው ትውልድ ታሪክ ዘካሪ፣ ታሪኩን በጥበብ አኗሪ፣ ጠላቶቹ እየገፉት የሚወድቁ፣ እየነኩት የሚያልቁ፣ ገፍተው የማይጥሉት፣ ችለው የማያጎድሉት፣ ተዋግተው የማያሸንፉት፣ ተሟግተው የማይረቱት፣ ሮጠው የማይቀድሙት፣ ጎትተው የማያስቆሙት ነው፡፡
ትዕግስት፣ ጽናትና እመነት ያለው፣ ፍቅርና ክብር የተቸረው፣ ጀግንነት የታደለው፣ ከአመነ የማይከዳ፣ ከገጠመ የማያወላዳ ድንቅ ሕዝብ፡፡ ከነብሱ በላይ የሚወዳት፣ በልቡ መንበር ውስጥ ያስቀመጣት፣ ከደሙ ጋራ ያዋሃዳት፣ በሰማይም መምድርም በስስት የሚመለከታት፣ ከምንም ከማንም ጋር የማያነጻጽራት፣ ከፍ አድርጎ የሚያከብራት፣ ራሱን ሰጥቶ የሚኖርላት፣ ተዋድቆ የሚያስከብራት ሠንደቁ ተነካች ሲባል ይከፋል፤ በሚወዳት ምልእክቱ የሚመጡበትን አይምራቸውም፣ የሚያጎርሳው እጁ ነፍጥ ያነሳል፣ እርፍ የጨበጠው ክንዱ ይተኩሳል፡፡

ጠላቶች በየዘመኑ ሞከሩት፣ ነካክተው አስቆጡት፣ በክብሩ መጡበት፣ ስለ ክብር ገጠማቸው፣ በጀግንነቱ ጣላቸው፣ ሁሉንም እንዳልነበር አደረጋቸው፡፡ የመጡበት እስኪጠፋቸው፣ የተወለዱበት ቀን እስኪያስጠላቸው፣ በእፍኙ ገብተው ምጥ እስኪይዛቸው ድረስ አስጨነቃቸው፣ ጀግና ነውና ቀጣቸው፤ ፍርድ አዋቂ፣ የተጣላን አስታራቂ፣ የታመመን ጠያቂ፣ ተራማጅ ሀሳብ አፍላቂ፣ የተጣመመን አራቂ ነው አማራ፡፡
ምድርን በጥበቡ አስሷታል፣ ጥበብን ተከትሏታልና መንገዱ ሁሉ በጥበብ ነው፡፡ ያልወጣበት የዘመን ተራራ፣ ያልተሻገረው መከራ የለም፡፡ ሳይነካቸው የነኩት፣ ሳይጠራቸው የመጡት ጠላቶቹ በአንድ ጀንበር ጥሏቸው፣ ክንዱን አሳይቷቸው፣ የዘመናት ሕልማቸውን ባዶ አድርጎባቸው፣ ጀንበራቸውን አጥልቆባቸው፣ የራሱን ጀንበር ሲያበራ፣ መንገድ የጠፋባቸውን ሲመራ፣ አንገት የደፉትን ሲያኮራ፣ በጨለማ ውስጥ የነበሩትን ወደ ብርሃን ሲመራና ሲጠራ ያዩት ሁሉ ደነገጡ፣ በሀዘንም ተዋጡ፣ ክንዱ ከበዳቸው፣ ግርማው አጠፋቸው፡፡
በጀግንነቱ ዓለም ተደነቀ፣ ፈሪም ተጨነቀ፣ ይህስ እንደምን ይኾናል፣ እንዴትስ ኾነ? ሲልም ጠየቀ፡፡ ሌላ እድል መሞከራቸው አልቀረም፣ ዳግም ሊገፉት፣ ቢቻላቸውም ሊያጠፉት መጡበት፣ ከጀግንነቱ ሳይጎድል ጠበቃቸው፣ ክንዱን አሳያቸው ዳግም ቀበራቸው፡፡ የተመኟት ሀገር፣ የቀመሩት ቀመር፣ ያሰመሩት መስመር፣ ያዘጋጁት የግዞት ቀንበር ሁሉ እንደ ጉም በኖ እንደ ጭስ ተኖ ጠፋ፡፡
በአያሌ ፈተናዎች ተፈትኖ ያለፈው ሕዝብ ዛሬም ሌላ ፈተና ገጥሞታል፣ ፈታኙም አቅፎ ወንዙን ያሻገረው፣ እንደ ካብ አጥር ኾኖ ያኖረው፣ ከበረሃ አውጥቶ የሾመውና የሸለመው፣ ምራ ብሎ ሀገርን ያክል ታላቅ እመነት፣ ሕዝብን ያክል ታላቅ እውነት የሰጠው ቡድን ነው፡፡ ይህ እኩይ የሆነ ቡድን በአጎረሰው ነክሶታል፣ በተዋጋለት ወግቶታል፣ በሞተለት ገሎታል፣ በደገፈው ገፍቶታል፡፡ አሸባሪው ትህነግ አማራን ያጠፉልኛል ያላቸውን የክፋት ደረጃዎች ሁሉ ተጠቅሟል፡፡

ዳሩ በሚፈራውና በሚጠላው ሕዝብ ከተቀመጠበት ዙፋን ወርዷል፣ አያልቅም ያለው የስልጣን ዘመን አልቋል፣ እንዳልነበር ኾኖ ፈራርሷል፡፡ ሞት ላይቀር ጣረሞት እንዲሉ በጣር ውስጥ ኾኖም የሚጠላውን ሕዝብ መውጋት ጀምሯል፡፡ ታዲያ አማራም የተቃጣበትን ጥቃት ለመመከት በመትመም ላይ ነው፡፡
ʺያ ጀግና ተነሳ ትጥቁን አሳምሮ ሳንጃውንም ስሎ
የሀገሬን ክብሬ አላስነካም ብሎ” ለክብርና ለሀገር ሲል ጮማ ባጎረሳቸው እጁ እርሳስ ሊጨምርላቸው ትጥቁን እያሳመረ ዘመቻ ላይ ነው፡፡ ለወገን የማይራሩ፣ በጥፋታቸው የማያፍሩትን ሁሉ ይቀጣቸዋል፡፡
አማራ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከልክ ያለፈ ትዕቢቱና ክፋቱ ሲበዛ በሰላም ይተው ዘንድ ለምኖት ነበር፡፡ መላ ኢትዮጵያዊያንም እባክህን ብለውት ነበር፡፡ አሸባሪው ትህነግ ግን ከክፋቱ የመመለስ ሀሳብም ፍላጎቱም አልነበረውም ይልቁንስ እያደር እየጨመረበት ሄደ እንጂ፡፡
ʺምን ያደርግልሃል ከነገር ላይ ነገር
ብንኖር ይሻላል በአደግንበት መንድር” አለው አማራ፡፡ ከነገር ላይ ነገርህን ተዎን፣ በማንነታችን፣ በቀያችንና በመንደራችን እንኑር ተወኝ ካለው ቆይቷል፡፡ እርሱም ተቆጥቶ ነፍጥ ያነሳ ቀን የሚመጣውን አይቋቋመውም እና ተው ብሎት ነበር፡፡ አብረን እንኑር፣ ሰፊ ሀገር፣ ዘመናትን ያሻገረ ፍቅር እያለ ነገርህን ተው፣ ከመለያዬት መገናኜት፣ ከጠላትነት ወንድማማችነት ይሻላልም አለው፣ እርሱ ግን አይኾንም አለ፣ ይባስ ብሎ አርፎ በተቀመጠበት ጥቃት ከፈተበት፡፡
ʺአንበሳውን ነኩት እነ ልክ አያውቁ
ምን እንደሚያመጣ ቀድመው ሳይጠይቁ” አንበሳውን ነካኩት፣ ከምሽጉ ቀሰቀሱት፣ ተቆጥቶ እንዲነሳ ገፋፉት፣ ቀድመው አለመጠየቃቸው፣ ምን ሊያደርግ እንደሚችል አለመተንበያቸው የማይደፈረውን ደፈሩት፣ አሁን አንበሳው ተነስቷል፣ ክንዱን አንስቷል፣ አንበሳን ማን ያሸንፋል፣ ማንስ ችሎ ከፊቱ ይቆማል፡፡
ጠላቶችህ የሚበዙት ስለሚፈሩህ፣ በጀግንነትህ ስለሚቀኑብህ ነው፡፡ ʺሃይማኖት የእግዚአብሔር ገንዘብ ነው፣ ሀገር ግን የሁሉ ነው፣ በዚሕ ዓለም ሰው ሁሉ ያለበት ታላቅ ዕዳ ታማኝነት ነው፡፡ አንድነት በደስታም ሆነ በችግር ጊዜ ጠቃሚ ነው” እንዳሉ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኀይለ ሥላሴ ለጋራ ሀገር፣ በታማኝነትና በአንድነት በደስታም በመከራም ጊዜ ከቆሙ ጠላት አይዳፈርም፣ ቢዳፈርም ተሸንፎ ይመለሳል፣ በአንድነት ክንድ ይጠፋል፡፡ አንድነት የሁሉም መሠረት ነውና፡፡
ʺሽንብራዬ አፈራች ከእንግዲህ ልጠርጥር
ጅል እዳ ይገባል በጠገበ ቁጥር ” እንዳለ ጅል በጠገበ ቁጥር እዳ ውስጥ ይገባል፣ የአሸባሪው ትህነግ ጥጋብም እዳ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ አሁን ላይ መፈናፈኛ የለውም፡፡ ጀግኖቹ ዙሪያውን ከበውታል፣ ከልክ ያለፈ ጥጋብ ሞትን ይጠራልና ሞት ጠርቶታል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
