“በጠላቶቻችን የተደቀነብን የህልውና አደጋ በጣጥሰን ለመሻገር ሁሉም ዜጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ መተባበር ፣ ጠላት ከሚነዛው አሉባልታ ወሬ ራስን መጠበቅ ፣ አንድነታችንን እና ሕብረታችንን ማጠናከር ወቅቱ የሚጠይቀው ዐብይ ጉዳይ ነው” መከላከያ ሚኒስቴር

156

“በጠላቶቻችን የተደቀነብን የህልውና አደጋ በጣጥሰን ለመሻገር ሁሉም ዜጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ መተባበር ፣ ጠላት ከሚነዛው አሉባልታ ወሬ ራስን መጠበቅ ፣ አንድነታችንን እና ሕብረታችንን ማጠናከር ወቅቱ የሚጠይቀው ዐብይ ጉዳይ ነው” መከላከያ ሚኒስቴር

ባሕር ዳር:ሐምሌ 23/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ)የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በማኅበራዊ የትስስር ገጹ ባወጣው ጽሑፍ እንዳለው የውስጥና የውጭ ጠላቶች የሕዝቡን ሥነ-ልቦና ለመስለብና የተፈጠረውን አንድነት ለማፍረክረክ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሥነ-ልቦና ጦርነት አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ በሚችለው ሁሉ ከሠራዊቱ ጎን በመቆም “ኢትዮጵያ ፈረሰች” ብለው ያሻቸውን በሕዝቡ ላይ ለመፈፀም ያሰፈሰፉ የውስጥ ቅጥረኞች፣ ባንዳዎች እና የኢትዮጵያ ልማት የራሳቸው ጥፋትና ውድቀት የሚመስላቸው የውጭ ጠላቶችን በማሳፈር ላይ ይገኛል ነው ያለው፡፡

“ሕዝባችን የሠራዊታችን የማይነጥፍ አስተማማኝ ደጀን በመሆን በሎጂስቲክስ ድጋፍ ፣ ከዳር እስከ ዳር በመነቃነቅ በሰው ኀይል ሠራዊታችንን በማጠናከር ታሪካዊ ሀገርን የማዳን ሥራ እየሠራ ነው፤ ለዚህም የሕዝባችን የማይነጥፍ ድጋፍ የድላችን ቁልፍ በመሆኑ እናመሰግናለን” ብሏል።

በጠላቶች የተደቀነውን የህልውና አደጋ በጣጥሶ ለመሻገር ሁሉም ዜጋ ከመቼውም ግዜ በላይ መተባበር ፣ ጠላት ከሚነዛው አሉባልታ ወሬ ራስን መጠበቅ ፣ አንድነትን እና ሕብረትን ማጠናከር ወቅቱ የሚጠይቀው ዐብይ ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

በመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ የታየው ሕብረትና በአንድነት መቆም ጠላቶችን አስደንግጧል ሚኒስቴሩ የአሸባሪው ጁንታ ጎራ በፍርሃት እንዲርድ አድርጓል ብሏል፡፡

የሕዝቡን አንድነትና ፅናት ለመሸርሸር ጠላት እየፈበረከ የሚረጨው አሉባልታዎችን መከላከል ፣ ሳያውቁ ጠላት ኾን ብሎ የሚለቀውን አሉባልታ በመቀባበል የጠላት ወኪል የሚሆኑ ወገኖችን መምከር ፣ መገሰፅ እንደሚያስፈልግም አስገንዝቧል፡፡

በአሸባሪው ሕወሓት እየተፈበረኩ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚረጩ የውሸት መረጃዎችን ፣ በየአገልግሎት መስጫዎች የሚነዙ አሉባለታዎች ፣ ስለ ሠራዊቱ የግዳጅ ውሎ ሰው የሚቀባበለው ወሬ ለጠላት ግብዓት የሚሆኑና የወገንን እንቅስቃሴን የሚጎዱ መሆኑን አሳስቧል።

በዚህም:-

1. የመረጃ ምንጩ ያልታወቁ ቀልብ የሚስቡ መረጃዎችን ከማጋራት መቆጠብ፤

2.የሠራዊቱን ከቦታ ቦታ እንቅስቃሴ ፣ የሚጓጓዙ የጦር መሳሪያዎች አይነትና ብዛት፣ የሎጂስቲክስ ድጋፍ እንቅስቃሴዎችን ፎቶ በማንሳት በማኅበራዊ ሚዲያ አለመለጠፍ ፡፡ ይህን የሚፈፅም ከተመለከቱም ማስቆም፡፡ ፍቃደኛ ካልሆነ ለጸጥታ ኀይሎች ወዲያው መጠቆም፡፡

3. በመንግሥት በተወሰነው የተናጠል ተኩስ አቁም ወቅት የሚደረግ የጠላትን ትንኮሳ መከላከል ሥራ በማኅበራዊ ሚዲያ አለመለጠፍ፤

4. አንዳንድ ዩ-ቲዩበሮች ለሽርፍራፊ ሳንቲም በሚል ሰበር ! በሚል ምንጩ ያልታወቀና ያልተረጋገጠ አሉባልታ በመንዛት የወገንና የሀገርን ጥቅም አሳልፎ ለጠላት አለመስጠት፤

5.ወቅታዊ ወታደራዊ እንቅስቃሴን በሚመለከት በታወቀ መንግሥታዊ ወይም በሚመለከተው የመከላከያ ኀላፊ ወይም አዛዥ ያልተሰጠ መረጃ ከሆነ አንመን ፣ አናጋራ፤

6.ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ በሠራዊቱ ግዳጅ አፈጸጸምና በሕዝቡ ሞራልና ሥነ-ልቦና የበላይነት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩና ጠላት ኾን ብሎ የሚለቃቸውን መረጃዎች ባለማሰራጨት እንተባበር ሲል ሚኒስቴሩ ጠይቋል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየኪነ-ጥበቡ ማኅበረሰብ ሀገር የማዳን ዘመቻውን በሙያው እንዲያግዝ የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ጥሪ አቀረቡ።
Next articleʺአንበሳውን ነኩት እነ ልክ አያውቁ ፣ ምን እንደሚያመጣ ቀድመው ሳይጠይቁ”