በሀገሪቱ የቫይረሱ ስርጭት 4 ነጥብ 9 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡

344

ባሕር ዳር፡ መስከረም 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰውን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መገናኛ ብዙኃንና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡

ኤች አይ ቪ/ኤድስ በኢትዮጵያ ያለውን ከፍተኛ መስፋፋት ለመግታት የግንዛቤ ፈጠራ ላይ ለመስራት እንዲያግዝ ለመገናኛ ብዙኃን እና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በአዳማ ስልጠና እየተሰጠ ነው። የፌዴራል ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያ አና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ነው ስልጠናውን እየሰጠ የሚገኘው፡፡ ከስልጠናው በኋላም ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ኅብረተሰቡ ስለ ኤች አይ ቪ/ኤድስ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችሉ ዘገባዎች በበቂ ደረጃ እንደሚተላለፉ ይጠበቃል፡፡

ጥራቱን የጠበቀ እና ቀጣይነት ያለው የመድኃኒት እና የተዛማጅ ግብዓቶችን አቅርቦት ለማረጋገጥ በ2012 ዓ.ም የአሰራር ሥርዓቱን እንደሚያጠናክር የመቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡ በተያዘው ዓመት 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎችን የኤች አይ ቪ ምርመራ እና ምክር አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ ያወቁ ሰዎችን ምጣኔ ከ90 በመቶ በላይ ለማድረስ ማቀዱንም የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ገብረመድኅን ተናግረዋል።

ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የሁለተኛ ደረጃ እና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች የሚበዙባቸው ፕሮጀክቶች ሠራተኞችን የሕይወት ክህሎት ትምህርትና ስልጠና መስጠት ከቅድመ መከላከል ሥራዎች አንዱ እንደሆነም ነው የተመላከተው። በዚህ ወቅት በአማራ ክልል የስርጭት ምጣኔው 1 ነጥብ 2 በመቶ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡ ከፍተኛ የስርጭት ፍጥነት እንዳለበት የተመላከተው የጋምቤላ ክልል ደግሞ 4 ነጥብ 9 በመቶ መድረሱ ተነግሯል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በገጠር ዜሮ ነጥብ 4፣ በከተማ 3 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ አማካይ የስርጭት መጠኑ ዜሮ ነጥብ 9 በመቶ ነው።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን – ከአዳማ

Previous articleሰባት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ወርቅና የዉጪ ሀገራት ገንዘቦች ተያዙ፡፡
Next article‹‹አጋጣሚው ከሥራ ዕድል ፈጠራ በዘለለ የወሎን ሕዝብ ከፍታ ለአምባሳደሮቻችን የምናሳይበት መልካም ዕድል በመሆኑ በቂ ዝግጅት አድርገናል፡፡›› የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ