
”የውስጥ ባንዳዎች ከውጭ ጠላት ጋር በመተባበር ሀገሪቱን ለማፍረስ የሚያደርጉትን ሴራ በተባበረ ክንድ መመከት ያስፈልጋል“ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ እንድሪስ አብዱ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይልን እና ሚሊሻ የሚደግፍ እና ሽብርተኛውን ትህነግ የሚያወግዝ ሰልፍ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳድር በከሚሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ የከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች የትህነግ ጁንታ ቡድን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠላት ነው ብለዋል፡፡
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ “በሉዓላዊነታችን ተደራድረን አናውቅም ታሪካችን ምስክር ነው፣ የመከላከያ ሠራዊታችን የሉዓላዊነት ምልክታችን ነው” የሚሉ እና ሌሎች መልእክቶችም በሰልፉ ላይ ተንጸባርቀዋል።

አሸባሪውን ትህነግ በሚያወግዘው በዚህ ሰልፍ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች የሃይማኖት አባቶች እና አባገዳዎች ተገኝተዋል።
በሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ እንድሪስ አብዱ “የውስጥ ባንዳዎች ከውጭ ጠላት ጋር በመተባበር ሀገሪቱን ለማፍረስ የሚያደርጉትን ሴራ በተባበረ ክንድ መመከት ያስፈልጋል” ብለዋል።
ኅብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።
ዓለምአቀፉ ማኀበረሰብም የአሸባሪውን ትህነግ ሕፃናትን በጦር ሜዳ የመማገድ ጭካኔ በይፋ ማውገዝ አለበት ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ቤቴልሄም ሰለሞን-ከከሚሴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
