የወልድያ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ለውኃና መብራት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ምስጋና አቀረቡ።

258

የወልድያ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ለውኃና መብራት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ምስጋና አቀረቡ።

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለቱም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በተመሳሳይ ሰዓት በደንበኞቻቸው የወልድያ ከተማ ማኅበረሰብ አድናቆትንና ምስጋናን ተችረዋል።

ከተማዋ የ5 ዋና ዋና ሀገር አቋራጭ አውራ መንገዶች መገናኛ ናት። ይህም ሁኔታ “መገናኛ” ከተማ የሚል ቅጽል ስም አሰጥቷታል። ከተማዋ በህልውና ዘመቻው ከሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫ የሚነሱ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፤ የየክልሉ የጸጥታ ኃይሎች፤ የክተት ዘመቻ ተሳታፊዎች እና ከትህነግ የሸሹ በርካታ ዜጎችን እያስተናገደች ትገኛለች።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት፣ ሁለቱም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ በወርኃ ክረምቱ ዝናብና ነፋስ በሚያይልበት ሰዓት፣ ውኃና መብራት ሳይቆራረጥ፣ ከእስከዛሬው በተሻለ ሁኔታ ተናበው የሚሰጡት አገልግሎት እንዳስደሰታቸው አስተያዬት ሰጭዎች ገልጸዋል።

አስተያዬት ሰጭዎቹ፣ ሁለቱም ተቋማት፣ የክተት ጥሪውን እንደተቀላቀሉ ነው የምንቆጥረው፤ ምክንያቱም ከእስከዛሬው በተለየ ሁኔታ፣ በጣም በርካታ የሀገራችን ዜጎች፣ ከተማችን ላይ በሚገኙበት በአሁኑ ሰዓት፣ የመብራት እና የውኃ ችግር አልተከሰተብንም፤ በዚህም በጣም ደስ ብሎናል። ይህንን አገልግሎት አሰጣጥ፣ ወደፊትም አጠናክረው እንዲቀጥሉ በማለት ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በነበረው የአሠራር ሒደታቸው፣ በመብራት ኃይል በኩል የመብራት ምሰሶ ወደቀብኝ፣ በውኃና ፍሳሽ አገልግሎት በኩል ደግሞ የመብራት መጥፋት እና የመብራት ኃይል አለመመጣጠን ችግር ፓምፕ ተቃጠለብኝ በሚል ምክንያት የመብራትና የውኃ መቆራረጦች ይስተዋሉ እንደነበር የወልድያ ከተማ ኮምዩኒኬሽን አስታውቋል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየወገኑ ሞት ልቡን ቢያስከፋው ፣ እንደ ጥራጊ ዘቅዝቆ ደፋው
Next articleየክተት ጥሪው ህልውናን የማስቀጠል አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን በመገንዘብ ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡