የወገኑ ሞት ልቡን ቢያስከፋው ፣ እንደ ጥራጊ ዘቅዝቆ ደፋው

368

የወገኑ ሞት ልቡን ቢያስከፋው
እንደ ጥራጊ ዘቅዝቆ ደፋው

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከ32 ዓመታት በላይ ታግለው ያሸነፉ የአሸባሪው ትህነግ ቡድን ማርከሻ ናቸው። ባለታሪካችን የአርበኝነት ተጋድሏቸውን ያህል አልተነገረላቸውም። ከፋኝ መስርቶ በርሃ ከመግባት እስከ የወልቃይት ሕዝብ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴነት ታግለው አታግለዋል፣ ምሽግ ደርምሰው የኢትዮጵያን ሕዝብ ጠላት ላይመለስ ሸኝተዋል። የስርቆት መብል ያሳበጠውን፣ ፈርጣማ ክንዱን በሕዝብ ላይ ያሳረፈውን፣ የማይከሰስ ኾኖ ባዘጋጃቸው ጅምላ መቃብሮች ዘር ለማጥፋት የዘመተውን የፋሽስት ውላጅ የባንዳዎች ስብስብ ከ1981 ዓ.ም ጀምረው በመታገል ተደጋጋሚ ድል ተቀዳጅተዋል።

ታጋይ መብራቱ ጌታሁን የተወለዱት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ምድር ነው። እድገታቸውም የአካባቢው ሰዎች ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ነጻነታቸውን ለማስከበር ያደረጉትን ተጋድሎ እየተመለከቱ ነው። እድሜያቸው በደረሰ ጊዜም ከፋኝ መስርተው ጫካ በመግባት ከትህነግ ጋር ትግል አድርገዋል። ትህነግ በሕዝብ ጫንቃ ስልጣን በተቆጣጠረ ማግስት ከወልቃይት ጠገዴ መሬት እንጂ ሌላውን አንፈልግም በማለት ሕዝቡን በግልጽና በስውር የመግረፍ፣ የማፈን፣ የመግደልና የመበደል ተግባሩን ተያይዟል። ታጋይ መብራቱም ክንዴን ሳልንተራስ፣ በአፍንጫዬ አፈር ሳይፈስ የአማራን ሕዝብ በደል አላይም በማለት አማራ ጠል የፖለቲካ አቋም ይዞ የተመሠረተውን የትህነግ ስብስብ ለመታገል ጫካ ገብተዋል።

ተደጋጋሚ የግንባርና የሽምቅ ውጊያ አድርገው በትህነግ ላይ ድል አስመዝግበዋል። በተለይ በቃብትያ ሁመራ በተደጋጋሚ ከባድ ውጊያ ተደርጎ አሸባሪ የትህነግ ቡድን ሽንፈትን ሲከናነብ እንደነበር አስታውሰዋል። በ1982 ዓ.ም ወልቃይትን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ መሬትን ለመቀራመት መሸንሸን ሲጀምር የሚመሩት የከፋኝ ቡድን ባደረገው ተጋድሎ አርሶ አደሩ በማሳው እንዲቆይ አድርጓል። ታጋይ መብራቱ ጠላትን በተደጋጋሚ በማንበርከኩም እንዲህ ተብሎ ተገጥሞለታል፡፡

የወገኑ ሞት ልቡን ቢያስከፋው
እንደ ጥራጊ ዘቅዝቆ ደፋው፣
ንቅንቅ የማይል ክንዱ አይዛባ
ደብልቆ እሚጥል እንደ ቁርባ
በ1982 እና 83 ዓ.ም በተለያዩ ቦታዎች ከትህነግ ጋር ከባድ ውጊያዎች አካሂደዋል። በወልቃይት በኩል ድል ማድረግ የተሳነው ትህነግ በወልድያ በኩል አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ሰኔ/1983 ዓ.ም ዳግም ፊቱን ወደ ወልቃይት ምድር አዙሯል።

ነገር ግን ከፋኝ ሕዝባዊ ድጋፍ ስለነበረው የትህነግን በትር በቀላሉ መክቷል፣ ግንባር ገጥሞም አሸንፏል። ይህ አልዋጥለት ያለው አሸባሪው የትህነግ ቡድን ታጋዮችን፣ ቅሬታ የሚያነሱ አርሶ አደሮችን እና ለመንገዴ እንቅፋት ይኾናሉ ያላቸውን ማፈንና ማጥፋት ተያያዘ። በዚህም ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ደብዛቸው የጠፉ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። በሂደቱ የተበሳጩት የከፋኝ አባላት በተለያዩ አካባቢዎች የሽምቅ ውጊያ ከፍተው በትህነግ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

ሶላ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ውጊያ ተካሂዶ በታጋይ መብራቱ የሚመራው ከፋኝ ድል ተቀዳጅቷል፣ ወፍ አርግፍ በተካሄደ ውጊያ ሙሉ በሙሉ በማሸነፍ ቦታውን ከመቆጣጠር አልፎ እስረኞችን እንዲለቀቁ አድርጓል፣ ቃብትያ ሁመራ ላይ ሁለት ጊዜ ከባድ ውጊያ ተደርጎ ከፋኝ አሸንፏል። እስረኞችን በማስለቀቅም ገሚሱ ታጥቆ ትግሉን እንዲቀላቀል አድርጓል። ሻንፈራ ተብሎ በሚጠራ ተራራ ላይ 24 ሰዓት የፈጀ ከባድ ውጊያ ተደርጎ በትህነግ ቡድን ላይ የማጥቃት ርምጃ ተወስዷል።

ከፋኝ በአከርና ማይካድራ ላይ ተመሳሳይ ድል በማድረግ የትህነግን ሰንደቅ ዓላማ አውርዶ ሕዝብ ያመነበትን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ አውለብልቧል። በሌሎች አካባቢዎች በተደረጉ ውጊያዎችም ትህነግ ተደጋጋሚ ሽንፈት ደርሶበት እንደነበር ታጋይ መብራቱ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውሰዋል።

ትህነግ መራሹ ቡድን የኢትዮጵያን መንግሥት ከመሠረተ በኋላ በተለይ በ1984 እና 85 ዓ.ም ሰዎችን በማንነታቸው እየለዬ ማሰር፣ መግደልና ማሰቃየቱን ሲቀጥል በኤርትራ በርሃ ኾነው ይታገሉ የነበሩት አርበኛ መብራቱ የትግል ስልት ለመቀየር ወሰኑ።

መንግሥት የሰጣቸውን ምህረት ተቀብለው ከሕዝብ ጋር በመቀላቀል የትህነግን ስርዓታዊ የጭቆና እንቅስቃሴ በመከታተል በርሃ ለቀሩት ጓደኞቻቸው መረጃ ማድረስ ጀመሩ። በዚህ ሥልት ዓመታት የፈጀ ትግል አካሂደዋል። በሂደቱ ከእርሳቸው ወገን ውስን ኀይል ቢጎዳባቸውም በትህነግ ላይ ግን ከፍተኛ ኪሳራ መድረሱን ነግረውናል። ታጋይ መብራቱ የወልቃይት ሕዝብን የአማራ ማንነት በማስመለስ እንቅስቃሴ በጉልህ ተሳትፈዋል።

በ2007 ዓ.ም ጎንደር ከተማ ‘የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት’ ኮሚቴ ሲመሰረትም የኮሚቴው አባል ናቸው። ከተመሠረተ በኋላም ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ ሕዝብ እንዲያውቀው በማድረግና ለትግሉ በማነሳሳት ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል ታጋይ መብራቱ። ኮሚቴው በ2008 ዓ.ም ጉዳዩን ይፋ በማውጣት ሕዝብ እንዲያውቅ አድርጓል። የማንነት ጥያቄው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲገባም ተደርጓል። በሕጋዊ አካሄዱ መሰረት መጀመሪያ ለትግራይ ክልል መንግሥት ማሳወቅ ቢኖርባቸውም የደኅንነት ስጋት ስላደረባቸው ቀጥታ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅንተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ወደ ትግራይ ክልል መሄድ የሚያስችል ሁኔታ ካመቻቸ በኋላም ታጋይ መብራቱ 10 ሰዎችን አስከትለው መቀሌ በመግባት አሳውቀዋል። በወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ከነበሩት ዓባይ ወልዱ ጋር በመገናኘትም በማመልከቻው ላይ አስፈርመዋቸዋል። ጉዳያቸውን አስፈጽመው ሁመራ ለማደር ባረፉበት ሆቴል ከሌሊቱ 5:30 ገደማ ታፈኑ፣ በዚህ ጊዜ መረጃው ለሕዝብ ደርሶ መላው የወልቃይትና የጎንደር ሕዝብ አመጽ ሊያስነሳ መኾኑ ሲታወቅ ከሌሊቱ 7:30 ገደማ በትህነግ ውሳኔ እንዲለቀቁ ተደርጓል።

በመንግሥታዊ ሥርዓት የታገዘው ጫና ቢበረታባቸውም አርበኛ መብራቱ ከጓደኞቻቸው ጋር በመኾን ትግላቸውን ቀጥለዋል። የኮሚቴው አባላት የሕዝብ ፊርማ አሰባስበው ድጋሜ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቀኑ። አርበኛ መብራቱን ጨምሮ ከፊሎቹ አዲስ አበባ የገቡት ቀድመው ነው። ሌሎች የኮሜቴው አባላት ግን አፋኝ ቡድን ተዘጋጅቶ ሱሉልታ ሲደርሱ ተያዙ። ይህንን የሰሙት ታጋይ መብራቱ ከአባላቱ ጋር በመኾን የሕዝብ ጥያቄ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት እየታፈኑ መኾኑን ለሕዝብ በማሳወቅ እንዲለቀቁ አድርገዋል።

ከዚያም ጥር 25/2008 ዓ.ም ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ባቀኑ ጊዜ የሚቀበላቸው ባለመገኘቱ ቀጠሮ ይዘው ተመለሱ። ያን ጊዜ ያልጠበቁት ነገር ከፊት ለፊታቸው ገጠማቸው።

ስብሀት ነጋ በሰጡት ቀጭን ትዕዛዝ አሸባሪ ተብለው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ገቡ። በጣቢያው ለቀረበላቸው ጥያቄ የሕዝብን ጥያቄ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሕጋዊ ኮሚቴ እንጂ አሸባሪዎች አለመኾናቸውን በማስረዳት ከአሠራር ውጪ ከምሽቱ 4:00 ከፖሊስ ጣቢያ እንዲወጡ ተደረገ። ነገር ግን እግራቸው ዳግም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ግቢን እንዳይረግጥ በማስፈራራት ነበር የለቀቋቸው። ታጋይ መብራቱን ጨምሮ የኮሚቴው አባላትን ከዓላማቸው የሚያቆም ምድራዊ ኀይል አልነበረምና በማግስቱ ሰዓታቸውን ጠብቀው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በመግባት ጉዳያቸውን አስፈጽመዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ – ከወልቃይት ጠገዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን የመልስ ምት የሚሰጥ እና ሴራውን የሚያጋልጥ ጠንካራ የመገናኛ ብዙኀን መገንባት እንደሚያስፈልግ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ውስጥ የሚሠሩ ጋዜጠኞች ተናገሩ፡፡
Next articleየወልድያ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ለውኃና መብራት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ምስጋና አቀረቡ።