
ኅብረተሰቡ ከአሸባሪዉ የትህነግ የሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በመጠንቀቅ የህልዉና ዘመቻው አካል እንዲኾን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ጥሪ አቀረበ፡፡
ባሕር ዳር:ሐምሌ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ ኢትዮጵያውያን በአንድነት መቆማቸውን ማኅበሩ አድንቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊ አርበኛ መንግሥቱ ወልደሥላሴ የሽብር ቡድኑ የተሰጠውን እድል ሳይጠቀም ዳግም ሕዝቡን ለባርነት ለመዳረግ ጥረት ማድረጉ የቆሸሸ ጥርቅም መኾኑን ያመላክታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር በተለያዩ የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ኾኖ ትግሉን በመቀላቀል ትህነግን ለመደምሰስ እየሠራ እንደኾነ ተናግረዋል።
“ትህነግ የሚያራምደው የሀሰት ፕሮፓጋንዳን የሚያሰራጩ የጁንታው ቅጥረኞችና አስመሳዮች ስላሉ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል” ብለዋል።
ወታደራዊ መረጃዎችን መስጠት ያለበት እራሱ ወታደራዊ ክፍሉ ነው እንጂ የወታደራዊ መረጃዎችን ከቅጥረኞች መስማት እንደማያስፈልግ ነው የተናገሩት።
ሌላው የግንባሩ ከፍተኛ መሪ ማተቤ አያና አሁን ላይ ሕዝቡ ከዳር እስከዳር መሳተፉ በታሪክ አባቶች ሲያደርጉ የነበረውን ተጋድሎ መድገሙን ያሳያል ብለዋል። ሀገር ከሌለ ሁሉም ስለማይኖር መሪም ኾነ ሕዝብ አንድ ኾነው በመናበብ ቡድኑን ሊታገሉ ይገባል ብለዋል።
የሽብር ቡድኑ ከውጊያ በላይ የሀሰት ፕሮፓጋንዳን እንደ ትልቅ ስልት እየተጠቀመ በመኾኑ መንግሥት በየወቅቱ መረጃን መስጠት አለበት ብለዋል። ትህነግን ብቻ ሳይኾን ሁሉንም ግብረአበሮቹን ማጥፋት እንደሚገባ አርበኛ ማተቤ አሳስበዋል።
አርበኛ ወርቁ በለጠ የተባሉት ሌላው የግንባሩ ከፍተኛ መሪ እንዳሉት አሸባሪው ትህነግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ካንሰር የኾነ ቡድን ነው ብለዋል። ሕልሙ ኢትዮጵያን አፈራርሶ የራሱን ፍላጎት ማሳካት ብቻ ስለኾነ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዚህ ወቅት ልዩነቶችን ወደጎን ትተው ሊታገሉት ይገባል ነው ያሉት።
የሽብር ቡድኑ ለራሱ እንዲመቸው ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳ በማድረግ ፍላጎቱን ብቻ ማሳካት ስለኾነ ኅብረተሰቡ በመደማመጥና ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ ትህነግን እንዲደመስሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
