የምዕራባዊያን ኢትዮጵያን የማዳከም ሴራ…

409

የምዕራባዊያን ኢትዮጵያን የማዳከም ሴራ…

ባሕር ዳር:ሐምሌ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሠሩት ሴራ የቅርብ ጊዜ ሳይኾን 200 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህራን ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ወደ ትናንሽ ሀገራት በመከፋፈል እና የውሸት ነፃነት በመስጠት የተዳከመች ሀገር ለመፍጠር ያልቆፈሩት ጉድጓድ እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ ታደሰ በቀለ ‹ከቀዳማዊ እስከ ቀዳማዊ› በሚለው መጽሐፋቸው እንዳስቀመጡት ምዕራባውያን ኢትዮጵያን በዘውግ እና በሃይማኖት ወደ ትናንሽ ከፋፍሎ ለመበታተን ለረጅም ጊዜ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

በተለይም ደግሞ እንግሊዝ እና ጣሊያን ‹‹…የኢትዮጵያ ግዛት በጣም ሰፊ በመኾኑ እና በቋንቋና ባህል የተለያዩ ሕዝቦች የሚኖሩባት ሀገር በመኾኗ ተከፋፍለው የተለያዩ ሀገራት መኾን አለባቸው…›› በሚል የተለያዩ ጥናቶችን በማጥናት ለአውሮፓ መንግሥታት አቅርበዋል፡፡ እንግሊዞች ኢትዮጵያን ‹‹የትግሬ መንግሥት፣ የአማራ መንግሥት እና የኦሮሞ መንግሥት›› በሚል በመከፋፈል ተላላኪ መንግሥት እንዲያቋቁሙ የጥናት ሃሳባቸውን አቅርበው ነበር፡፡ ይህንም ጥናት ለአንዳንድ መንግሥታት አቅርበው “ኤርሳክን” እና “ብሮክስ አርስተን” የተባሉ እንግሊዛውያን በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብተው እንዲያጠኑ ተደርጎ ነበር።

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ መንግሥት ሚስጥሩ ተደርሶበት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ውለው ከሀገር እንዲውጡ ተደርገዋል፡፡ ሆኖም እንግሊዞች በራሳቸው ዜጎች ሳይሳካላቸው የቀረውን ፕሮጀክት ለማሳካት ባንዳዎችን በመጠቀም ያደረጉት ሙከራም ተደርሶበት ሊከሽፍ ችሏል፡፡ እንግሊዞች በዚህ ብቻ ሳያበቁ ‹‹ትግራይ ትግረኛ›› በሚል ትግራይ እና አፋርን ከኤርትራ ጋር ቀላቅለው እንዲገነጠሉ ሙከራ ቢያደርጉም አሁንም በማዕከላዊ መንግሥቱ ተደርሶበት ከሽፏል፡፡ ጣሊያንም ሀገሪቱን ‹‹የኤርትራ መንግሥት፣ የአዲስ አበባ መንግሥት፣ የኦሮሞ መንግሥት፣ የአማራ መንግሥት፣ የሲዳማ እና የሱማሌ መንግሥት እና የሀረር መንግሥት›› በሚል ሴራቸውን ለማሳካት አጥንተው ነበር፡፡ ይህንን ሴራም የአውሮፓ መንግሥታት እንዲያውቁት እና እውቅና እንዲሰጡት ጥረት አድርገዋል፡፡ ጥናቱንም በ1938 (እ.አ.አ) ‹‹ጊይዶ ዴል አፍሪካ ኦሬንታል ሃሊኖ›› ተብሎ በሚጠራው መጽሐፋቸው ጽሕፈው የዓለም ሕዝብ እንዲያነበው እና እንዲያውቀው አድርገዋል፡፡

ይሁን እንጅ ፈረንሳይ እና ኖርዌይ የኢትዮጵያን መከፋፈል በወቅቱ ተቃውመዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሴራ እና ተንኮል በሀገሪቱ ላይ እየተፈጸመ የሀገሪቱ መሪዎች እና ሕዝቦቿ በአንድነት የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ነፃነት አስከብረው ቆይተዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ቻላቸው ታረቀኝ እንዳሉት ምዕራባውያን ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይህን ዓላማቸውን ለማሳካት እንደ ጀምስ ብሩስ፣ ቶማስ ሙር፣ ክላውድ ማክሌ የመሳሰሉ ግለሰቦችን በቆንሲል እና በሚሲዮን የሽፋን ስም በተከታታይ ወደ ኢትዮጵያ በመላክ አስጠንተዋል፡፡ እ.አ.አ 1835 አንድ እንግሊዝ የፓርላማ አባል ወደ ኢትዮጵያ አቅንቶም፣ የሀገሪቱን ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ሀብት እንዲሁም የሕዝቡን ሥነልቦና ከተመለከተ በኋላ ሀገሪቱን ማዳከም ካልተቻለ በአፍሪካ ላይ ተሰሚነት እንደማይኖራቸው አቅርበው ነበር፡፡ የፓርላማ አባሉ የኢትዮጵያን የትምህርት ፖሊሲ በምዕራባውያን በመቀየር ባህሉን ጭምር መቀየር እንደሚገባ ፓርላማ ላይ አቅርቦ እንደነበር መምህር ቻላቸው ነግረውናል፡፡

እ.አ.አ በ1972 ሄነሪ ኪሲንገር የተባለው አሜሪካዊም “ኢትዮጵያን ለማዳከም እና ለመበታተን ሁልጊዜ በጦርነት ማባዘን ይገባል›› የሚል ፖሊሲ ይፋ ማድረጋቸውን ነው መምህር ቻላቸው ያነሱት፡፡ በተለይም ደግሞ ከ1930ዎቹ ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመበተን ዘውግ እና ሃይማኖትን እንደ ዋነኛ ስልት አድርገው ሲጠቀሙ መቆየታቸውንም አንስተዋል፡፡ ምዕራባውያን ‹‹እ.አ.አ በ2030 ይፈራርሳሉ›› ብለው ካስቀመጧቸው የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ እና ናይጀሪያ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡

በቅርቡም ኢትዮጵያ የውጭ ድጋፎችን እንዳታገኝ መከልከል፣ ባልተረጋገጠ እና ሚዛኑን ባልጠበቀ መረጃ ላይ ተመርኩዞ በሀገሪቱ ላይ የሚዲያ ዘመቻ ከፍተው ሀገሪቱን ለማፈራረስ እየሠሩ እንደኾነም በማሳያነት አንስተዋል፡፡

ከሕዳሴው ግድቡ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ የግብጽን እና የሱዳንን ሀሳብ እንድትቀበል አሜሪካ ያሳየችው ጣልቃ ገብነትም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ለመበተን ያነሳሳቸው ምክንያት ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ፣ የራሷ ፊደል እና የራሷ የዘመን አቆጣጠር ያላት ከጥንት ገናና ሀገራት መካከል አንዷ መኾኗ እና የምዕራባውያን ስፔስ ሳይንስ መሰረት በመኾኗ ያ የጥንት ስልጣኔ እንደገና ማንሰራራት ከቻለ የጥቁር የበላይነትን ሊያመጣ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አንስተዋል፡፡

በተለይም ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ከኤርትራ እና ከቀጠናው ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣትን ተከትሎ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን አንስተዋል፡፡

መምህር ቻላቸው ምዕራባውያን ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የሚሠሩ መሪዎችን ለማስወገድ በትኩረት እንደሚሠሩም ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም በስልጣኔ ቀደምት የነበሩ ሀገራት ኢላማ መኾናቸውን ነው መምህሩ ያነሱት፡፡ ለዚህም ሱኒ እና ሽሃ በሚል ኢራቅ ላይ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ከዚያም አልፎ ሶሪያ፣ ሊቢያ እና በመሳሰሉ ሀገራት ላይ ተግባራዊ መደረጉን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

አሸባሪው ትህነግም በአሁኑ ወቅት የምዕራባዊያን ጉዳይ አስፈጻሚ ኾኖ እያገለገለ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጥንት ጀምሮ በሀገሪቱ ላይ የሚሠራውን ደባ ተረድቶ ብሔራዊ አንድነቱን ማጠናከር እንደሚገባው መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
XMA Header Image

Previous articleየወልድያ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች የአካባቢያቸውን ጸጥታ በንቃት እየጠበቁ መሆኑን ገለጹ፡፡
Next articleኅብረተሰቡ ከአሸባሪዉ የትህነግ የሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በመጠንቀቅ የህልዉና ዘመቻው አካል እንዲኾን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ጥሪ አቀረበ፡፡