
ባሕር ዳር፡ መስከረም 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) ትናንት በካምፕ ኑ የላሊጋውን 6ኛ ሳምንት ጨዋታ ከቪላሪያል ጋር ያደረገው ባርሴሎና ከእረፍት መልስ ሊዮኔል ሜሲን በታፋ ጉዳት ምክንያት አጥቷል፡፡
ከጉዳት መልስ ትናንት ለባርሳ ለ 400ኛ ጊዜ የተሰለፈው ሜሲ ያጋጠመው ጉዳት መጠነኛ መሆኑን አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡ በጨዋታው ባርሴሎና 2ለ1 በሆነ ጠባብ ውጤት ቪላሪያልን ሲያሸንፍ ግቦቹን ግሪዝማንና አርቱር በ6ኛውና በ15ኛው ደቂቃ አስቆጥረዋል፡፡ የቪላሪያልን የማስተዛዘኛ ግብ ደግሞ ሳንቲ ካዞርላ ነው ያስቆጠረው፡፡ ውጤቱን ተከትሎም ባርሴሎና ደረጃውን በ10 ነጥብ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ አድርጓል፡፡ በላሊጋው ሌሎች የምሽት ጨዋታዎች ሪያል ቫላዶሊድ ግራናዳን በሜዳው አስተናግዶ አንድ እኩል ሲለያይ ሪያል ቤትስ ሌቫንቴን 3ለ1 አሸንፏል፡፡
በምሽቱ ጨዋታ ነጥብ የተጋራው ግራናዳ ላሊጋውን በ11 ነጥብ ይመራል፤ አትሌቲክ ቢልባኦ እና ሪያል ማድሪድ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በእኩል 11 ነጥብ 2ኛና 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
በእንግሊዝ ካራባኦ ዋንጫ ደግሞ ቶተንሀም ሆትስፐር በሊግ ሁለት በሚጫወተው ኮልቸስተር ዩናይትድ በመለያ ምት 4ለ3 ተሸንፏል፡፡ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 0ለ0 በማጠናቀቃቸው ነበር ሁለቱ ቡድኖች ወደ መለያ ምት ያመሩት፡፡ በመጨረሻም የታችኛው ሊግ ቡድን አሸናፊ ሆኗል፡፡

በምሽቱ ሌሎች ተመሳሳይ መርሀ ግብሮች አርሰናል ኖቲንግሀም ፎረስትን 5ለ0፣ ሳውዝአምተን ፖርትስማውስን 4ለ0፣ ሌሲስተር ሲቲ ሉቶንን በተመሳሳይ 4ለ0፣ ማንቸስተር ሲቲ ፕሪስተንን 3ለ0 አሸንፈዋል፡፡ ኤቨርተንም ሼፊልድ ዌይንስዴይን 2ለ0 ረትቷል፡፡
በጣልያን ሴሪ ኤ ጁቬንቱስ በጠባብ ውጤት አሸንፎ የደረጃ ሰንጠረዡን መምራት ጀምሯል፡፡ ትናንት ምሽት በተካሄዱ የ5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ጁቬንቱስ ብሪሽያን 2ለ1 ሲያሸንፍ ሄልሳ ቬሮና ከዩዲኒዜ ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ጁቬንቱስ በጠባብ ውጤት አሸንፎ ሴሪኤውን በአንድ ነጥብ ብልጫ በ13 ነጥብ መምራት ጀምሯል፤ የ5ኛ ሳምንት ጨዋታውን ያላካሄደው ኢንተርሚላን በ12 ነጥብ ይከተላል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ
በአብርሃም በዕውቀት