ብዙኅን መገናኛ ተቋማት የኢትዮጵያን እውነት ለቀሪው ዓለም ለማስተዋወቅ በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ጠቆሙ፡፡

135
ብዙኅን መገናኛ ተቋማት የኢትዮጵያን እውነት ለቀሪው ዓለም ለማስተዋወቅ በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ጠቆሙ፡፡
 
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዘመነ ሉላዊነት በርካታው ሕዝብ ስለዓለም ሀገራት ያለው ግንዛቤ ምንጩ ብዙኀን መገናኛ ተቋማት ናቸው፡፡ ሀገራትን በክፉም ይሁን በደጉ በማስተዋወቅ በኩል ደግሞ የምዕራባውያን ሀገራትን ብዙኀን ተቋማት የሚያክል የለም፡፡ ስለአፍሪካ ሕዝብ በድህነት መኖር ለራሳቸው ለአፍሪካውያን ሳይቀር አጋነው እና አጉልተው የሚነግሯቸው የምዕራባውያን ብዙኀን መገናኛ ተቋማት ናቸው፡፡
 
መካከለኛው ምሥራቅ የግጭት እና የሽብር ማዕከል ተደርጎ በበርካታው ሕዝብ ዘንድ የተሳለው ብዙኃን መገናኛ ተቋማቱ በፈጠሩት የተጋነነ እና የተዛባ ስዕል ነው፡፡ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ ምንይችል እንግዳ እንደሚለው አሁን ላይ ብዙኀን መገናኛ ተቋማት በሀገር ውስጥ የሚያሳዩት የሃሳብ ብዝሃነት፣ ተደራሽነት እና ተዓማኒነት ተስፋ ሰጭ ነው፡፡ ዘመኑ የፈጠረውን የሚዲያ ቴክኖሎጂ በአግባቡ ተጠቅሞ መረጃን በፍጥነት በማድረስ እና ሀገራዊ አንድነትን በመፍጠር በኩል መሻሻሎች እንደሚታዩ ጠቅሷል፡፡
 
የኢትዮጵያን እውነት ለቀሪው ዓለም በማስተዋወቅ በኩል ግን ገና ብዙ ይቀራል ባይ ነው፡፡ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት በተመረጡ ቋንቋዎች፣ በተመረጡ ይዘቶች እና በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይኖርባቸዋል ብሏል ጋዜጠኛ ምንይችል፡፡
 
አሁን ላይ የሚስተዋለው ዲፕሎማሲያዊ ጫና የኢትዮጵያን እውነት በአግባቡ ካለመረዳት የመነጨ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ አንዳንድ ሀገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የሚፈጥሩትን ጫና እና እኩይ ሴራቸውን ማጋለጥ ይገባል፤ ለዚህም ብዙኃን መገናኛ ተቋማቱ የኢትዮጵያን እውነት ማስተዋወቅ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ነው ያለው፡፡
 
ታላላቅ የዓለም ሀገራት መሪዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና ተቋማት ስለእያንዳንዱ ሀገር ያላቸው ግንዛቤ ምንጩ ብዙኃን ተቋማት ናቸው ያሉን ደግሞ የሥነ ተግባቦት ባለሙያው ነፃነት ተስፋዬ ናቸው፡፡ ስለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እውነት በመሪዎች እና በተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የሚያዙ አቋሞች መነሻ ብዙኀን መገናኛ ተቋማት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
 
አቶ ነፃነት የሀገር ውስጥ ብዙኀን መገናኛ ተቋማት የሀገራቸውን እውነት ለቀሪው ዓለም በማድረስ በኩል ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡ መንግሥት የዲፕሎማሲውን ሥራ ከማጠናከር ጎን ለጎን በተመረጡ ሀገራት እና ቆንስላዎች ቃል አቀባይ (የፕሬስ አታሼ) ቢኖረው ወቅታዊ መረጃ ለማድረስ እና አዝማሚያ ለማወቅ ይረዳዋል ብለዋል የሥነ ተግባቦት ባለሙያው፡፡ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም ከልማዳዊ አሠራር ወጥቶ ዘርፉ የሚጠይቀውን እውቀት እና ክህሎት የተላበሱ ዲፕሎማቶች እንዲኖሩ መደረግ አለበት ይላሉ፡፡
 
አሁን በውጭ ባሉ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የሚታዩት ጅምሮችም ተቋማዊ አሠራር ሊኖራቸው ግድ ይላል ባይ ናቸው፡፡ አቶ ነፃነት እንዳሉት የሀገር ውስጥ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት አንድ ሁነት ሲፈጠር ከሚያሳዩት ተነሳሽነት በዘለለ የኢትዮጵያን እውነት ለማስረዳት በእቅድ ላይ ተመስርተው በሰፊው ሊሠሩ ይገባል፡፡ እንግሊዝኛ እና አረብኛ ቋንቋዎችን ጨምሮ በሌሎች ቋንቋዎችም ጭምር የሀገር ውስጥ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት በውጭ ቅርንጫፎችን እስከመክፈት ድረስ አልመው መሥራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡
 
አስተያየት ሰጭዎቹ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትን ጨምሮ በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ሕግ የማስከበር ዘመቻ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ እስከ መግባት መድረሳቸውን አንስተዋል፡፡ ይህ ተፅዕኖ ኢትዮጵያን ካለማወቅ የመነጨ ስለሚሆን በተለይም ብዙኃን መገናኛ ተቋማት በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡
 
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
 
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
XMA Header Image
Previous articleአረብ ሊግ በህዳሴው ግድብ ላይ ያለውን አቋም እንደገና እንዲያየው ጥረት እንደምታደርግ አልጀሪያ አስታወቀች።
Next articleየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሕልውና ዘመቻው የሚውል ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ በዓይነት ድጋፍ ለአማራ ክልል አስረከበ፡፡