
አረብ ሊግ በህዳሴው ግድብ ላይ ያለውን አቋም እንደገና እንዲያየው ጥረት እንደምታደርግ አልጀሪያ አስታወቀች።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአልጀሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራማታን ላማምራ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ መግለጫውን የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የተመድ የሰላም እና የፖለቲካ ኮሚሽነር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የአረብ ሊግ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተሳሳተ አቋም እያራመደ መሆኑን ለአልጀሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራማታን ላማምራ ገለጻ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።
በዚህም የአረብ ሊግ አቋሙን እንደገና እንዲያየው ሀገራቸው ጥረት እንደምታደርግ የአልጀሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጸዋል።
አልጀሪያ ያላትን ግንኙነት እንደምታጠናክር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አልጀርስ እንዲበር ጥያቄ ማቅረባቸውን አምባሳደር ዲና አብራርተዋል።
የአፍሪካ G4 ተብለው የሚጠሩት ደቡብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ አልጀሪያ እና ናይጀሪያ የአፍሪካ ሚናቸውን በሚያጠናክሩበት ዙሪያም ከኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ጋር ውይይት አድርገዋል።
ኹለቱ ሀገራት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ስምምነት ማድረጋቸውንም አምባሳደር ዲና አስታውቀዋል።
አምባሳደር ዲና በትግራይ ክልል መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያደርግም በአሸባሪው ትህነግ በኩል ተቀባይነት አለማግኘቱን እና የሽብር ቡድኑ ዘመቻ በማድረግ ሰብዓዊ መብት እየጣሰ መሆኑን በመግለጫቸው አብራርተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው የባሕል እና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሂሩት ካሳው (ዶ.ር) ጀርመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እየሠሩ ያለውን ሀገር የማስተዋወቅ ሥራ በአካል ተገኝተው እንዳበረታቱም አንስተዋል።
ከሳውዲ አረቢያ 42 ሺህ ዜጎችን ወደ ሀገር መመለስ መቻሉንም ቃል አቀባዩ አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን-ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m