
አሸባሪው ትህነግ የሚያራምደው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮውን ለማሳካት በመሆኑ መረጃን ከታማኝ ምንጮች መውሰድ እና ደጋግሞ ማጣራት እንደሚገባ የሥነ ተግባቦት ምሁር አስገነዘቡ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የምንገኘው “በመረጃ ዘመን” ላይ ነው፡፡ መረጃ በዚህ ዘመን ወሳኝ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ መረጃ የዕውቀትም የኃይልም ምንጭ ነው፡፡ መረጃ ለግለሰቦች ሃብት፤ ለሀገር ደኅንነትም ዋስትና የመሆኑ ጉዳይ አያጠያይቅም፡፡ መረጃ በተለይም በጦርነት ወቅት ፈላጊዎቹ የመብዛታቸውን ያክል የመረጃ ነጋዴዎችም በርካቶች ይሆናሉ፡፡ የተዛባ መረጃ፣ ሐሰተኛ መረጃ፣ ያልተጣራ እና የተጋነነ መረጃ በብዛት ይሰራጫል፡፡ ትክክለኛውን መረጃ ማጣራት በዚህ ወቅት ፈታኝ እየሆነ መምጣቱም ይነገራል፡፡
የሥነ ተግባቦት ምሁራንም የብዙኃን መገናኛ ተቋማትን በጦርነት ወቅት “የመረጃ ርሃብተኞች ናቸው” ሲሉም ይገልጿቸዋል፡፡ ሉላዊነት እና ቴክኖሎጂ ለመረጃ ቅርበት ዓይነተኛ አስተዋፅዖ ያላቸውን ያክል ተጓዳኝ ችግሮችንም ይዘው መጥተዋል የሚሉት የሥነ ተግባቦት ባለሙያው አቶ ነፃነት ተስፋዬ ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ለተፈጠሩ ታላላቅ ችግሮች የተዛባ መረጃ ሥርጭት ምክንያት ነበር የሚሉት የሥነ ተግባቦት ባለሙያው አሜሪካ እና እንግሊዝ በኢራቅ እና ፕሬዚዳንቷ ሳዳም ሁሴን ላይ ያፈሰሱት መዓት ምንጩ ሐሰተኛ መረጃ ነበር ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ለተፈጠረው የሕልውና ችግር ዋናው ምክንያት “እኔ ያልኩት ብቻ” ይሁን የሚሉ ቡድኖችን በወቅቱ ካለማረቅ በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መልዕክቶችን ልጓም አለማበጀት ችግር እንደሆነም አቶ ነፃነት ይጠቁማሉ፡፡ የሽብር ቡድኖቹ ዲጂታል ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው የሐሰት መረጃ ማሰራጨትን አንድ የትግል ሥልት አድርገውታል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ነፃነት ገለፃ አሸባሪው ቡድን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር፣ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሂደት፣ በሕግ ማስከበር እና በሕልውና ዘመቻው ምክንያት ሆን ብሎ የተሳሳቱ መረጃዎችን ሲያሰራጭ ነበር፡፡ የተዛባ፣ የተጋነነ እና ስህተት የሆነ መረጃም መልቀቅን አንድ የትግል ስልት አድርጎ እየተጠቀመበት ነው ብለዋል፡፡
በበይነ መረብ ዘመን መረጃ ገንዘብም ጭምር በመሆኑ የሀገርን ሕልውና አደጋ ላይ እየጣሉ የግል ንግድ የሚያጧጡፉ ነጋዴዎች መኖራቸውንም ሕዝቡ መረዳት አለበት ነው ያሉት፡፡
የመከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ የሚያደርጓቸው እያንዳንዳቸው እንቅስቃሴዎች ወታደራዊ ኦፕሬሽን ነው ብለዋል አቶ ነፃነት፡፡ ይህንን በምስል እና በጽሑፍ በተለይም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማጋራት የሀገርን ደኅንነት አደጋ ላይ መጣል መሆኑ ሊታሰብበት ይገባልም ብለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ የሚያራምደው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮውን ለማሳካት በመሆኑ መረጃን ከታማኝ ምንጮች መውሰድ እና ደጋግሞ ማጣራት እንደሚገባ የሥነ ተግባቦት ባለሙያው አቶ ነፃነት ተስፋዬ አስገንዝበዋል፡፡ ይህንን የሚያጋሩ፣ አስተያየት የሚሰጡ እና የሚያሰራጩ አካላት ጉዳቱን ማሰብ ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት፡፡ ከኢትዮጵያውያን ሥነ ልቦና እና ከሙያዊ መርህ ውጭ መረጃ እና ምስል የሚለቁ ሰዎች የሚጎዱት ሕዝብን በመሆኑ እያንዳንዱን መረጃ ከሀገራዊ እና ማኅበረሰባዊ ፋይዳ አንፃር መቃኘት ይገባል ብለዋል፡፡
ትናንት እኛ እና በዙሪያችን ያሉ ሁሉ የሚያውቁትን እውነት አዛብተው የነገሩን የመረጃ ምንጮች በማናውቀው ጉዳይ ላይ ምን ያክል ሊዋሹን እንደሚችሉ በማሰብ መረጃን ከታማኝ ምንጮች መውሰድ እና ደጋግሞ ማጣራት ተገቢ እንደሆነም መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m