
ዐቃቤ ሕግ በእነ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ መዝገብ ጀነራል ገብረፃድቃን ገ/ትንሳኤን ጨምሮ በ74 ሰዎች ላይ ክስ መሰረተ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ ክስ የመሰረተዉ ተከሳሾች የፌዴራል መንግሥትን በኃይል ለመለወጥ በማሰብ በሽብርተኝነት ከተፈረጀዉ ከሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)አመራሮች ተልእኮ በመቀበል ጥቃት ለማድረስ የሚችል የትግራይ ማእከላዊ መንግሥት ወታደራዊ ኮማንድ በማደራጀትና በመምራት በትግራይ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ላይ በሚገኙ የሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በፌዴራል የመንግሥት ተቋማት ላይ እንዲሁም በአማራ እና በአፋር ክልሎች በተጨማሪም በኤርትራ ላይ ጥቃት በማድረሳቸዉ ነዉ፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በ 1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1)(ሀ)(ለ)፣ 33፣ 35፣38 እና የሽብርን ወንጀል ለመከላከል ለመቆጣጠር በ2012 ዓ.ም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀፅ 3(2) የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዉ በመገኘታቸዉ የሽብር ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል፡፡
ዐቃቤ ሕግ ክስን ያስረዱልኛል ያላቸዉን ከ500 በላይ የሰዉ ምስክሮችን፣ ከ5 ሺህ ገጽ በላይ የሆነ የሰነድ ማስረጃዎችን እንዲሁም የቴክኒክና የቪዲዮ ማሰረጃዎችን አያይዞ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡
ክሱ የቀረበለት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ተኛ የጸረ ሽብር ወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 272829 የሽብር መዝገቡ ተከፍቶ ጉዳዩን እየተመለከተው ይገኛል፡፡ መረጃው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ