
ሕዝቡ የህልውና ዘመቻውን እንዲቀላቀል መንግሥት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሙሉ ልብ እንደሚቀበሉት የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ በሚል በባሕር ዳር የክልሉ መንግሥት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ በመቀበል ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡
በሰልፉ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተወካይ አቶ ይደግ ማሩ ሕዝቡ ሽብርተኛው ትህነግ በአማራ ብሎም በኢትዮጵያ ላይ የደቀነውን አደጋ ለመከላከል በግንባር በመሳተፍ ላይ ለሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የየክልሎች ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ድጋፍ ለመስጠት በመሰባሰብ ያለውን አጋርነት በመግለጹ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
ሕዝቡ ለሠራዊቱ ደጀን መሆኑን ለማሳየት እና በተሳሳተ መረጃ የሽብር ቡድኑን የሚደግፉ የውጭ ኃይሎች ትክክል እንዳልሆኑ ለመግለጽ እና እውነታውን እንዲውቁት መልዕክት ለማስተላለፍ ሕዝቡ በጋራ መውጣቱ የሚመሰገን እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው እና ዘራፊው ትህነግ የከፈተው ጦርነት በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የተቃጣ በመሆኑ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመቻውን እንዲቀላቀል ያደረገውን ጥሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሙሉ ልብ እንደሚቀበሉት አስታውቀዋል፡፡ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነውን የትህነግ ሽብር ቡድን ከስሩ ተነቅሎ ሲጣል ብቻ ሀገር ሰላም እንደምታገኝ የጋራ ምክር ቤቱ ያምናል ብለዋል፡፡ ይህ ጦርነት ህልውናን የማስከበር የፍትሕ ጦርነት መሆኑን ነው ተወካዩ በመልዕክታቸው የገለጹት፡፡
አቶ ይደግ ሽብርተኛው ትህነግ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እና ለመበተን ሲኦል እንኳን ቢሆን መውረድን በመምረጥ ኢትዮጵያን ከማፈራረስ የቆየ ዕቅድ ካላቸው ጋር ግንባር ፈጥሮ ሲሠራ መቆየቱን እና እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
“ሽብርተኛው ትህነግ የኢትዮጵያ ክፉ አረም ነው፤ ነቀርሳ ነው” ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ይህ የጥፋት ቡድን ከምስረታው ጀምሮ በእኩልነት፣ በወንድማማችነት ተሳስሮ የሚኖረውን የአማራን ሕዝብ ጠላት አድርጎ ለመዋጋት መነሳቱን አንስተዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ በሁሉም ረገድ አንድ ሆኖ ተዋልዶ፣ ተዋዶ እና ተከባብሮ የሚኖረውን የአማራን እና የትግራይን ሕዝብ ለመለያየት የጥላቻ ግንብ ሲገነባ መቆየቱንም ተናግረዋል ተወካዩ፡፡ እናም ሽብርተኛው ትህነግ ፀረ ፍቅር ነው፤ ፀረ ሕዝብ ነው፤ ፀረ አንድነት ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መመስረት ዋና ዓላማ ሕዝብን ከህልውና ችግር ለመታደግ፣ ለነጻነት፣ ለእኩልነት እና ለፍትሕ መታገል በመሆኑ የመንግሥትን የክተት ጥሪ በሙሉ ልብ እንደሚቀበሉ እና ያለ ምንም ልዩነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድ በመሆን ወደ ግንባር እንደሚዘምቱ አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያን አረም በጋራ እንነቅላለን፤ ድል እናደርጋለን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለዓመታት ረፍት የነሳት ነቀርሳ የመነቀያው ጊዜ አሁን መሆኑን ነው ተወካዩ ያስታወቁት፡፡ ሁሉም ይዘምታል፤ ሁሉም ታሪክ ይሠራል ብለዋል፡፡ መንግሥት የጀመረውን የህልውና ዘመቻ በመደገፍ ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር እንደሚረባረቡ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡-የማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ