
“አባቶች የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ በጋራ ይሠሩ እንጂ ከመካከላቸው ባንዳዎች አልጠፉም ነበር፤ የእነዚያ ባንዳዎች ልጆች ናቸው ዛሬም ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር ለማፍረስ የመጡት፤ ወጣቱ ይኽን መረዳት አለበት” የአማራ ክልል ጀግኖች አርበኞች ማኅበር
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ ባይሳካለትም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሌሊት በጨለማ ቀን በብርሃን አይገቡት ጉድጓድ፣ አይወጡት ተራራ እየቧጠጠ መሆኑን ገልጿል ማኅበሩ፡፡ ይኸን ለመመከት ደግሞ በጋራ እና በመተባበር መሥራት ተገቢ መኾኑን የአማራ ክልል ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ሊቀመንበር ዳኝነት አያሌው ከአሚኮ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ አሳስበዋል፡፡ አቶ ዳኝነት ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ተጋድሎ ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር ናት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን በርካታ ሀገራት ቅኝ ተገዥ ለማድረግ የተለያዩ መንገዶችን ቢጠቀሙም በልጆቿ ተጋድሎ አንድነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር መኾኗን ዓለም ሊረዳ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ ሊቀመንበሩ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮቿን ተሻግራ በእድገት እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፤ የእናት ጡት ነካሾች ዛሬም የጥቃት እጃቸውን እየዘረጉ ቢሆንም ወጣቱ የአባቶቹ ልጅ ነውና ታሪክን እየደገመ ነው፤ ለዚህ ማሳያው ደግሞ የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቅ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተገባዶ ኹለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መፈጸም ማሳያዎቿ ናቸው፡፡
ነገር ግን እድገቷ ያልተዋጠላቸው የውስጥ ጠላቶቿ ጦር ሠብቀው፣ ጠመንጃ አንግበው ለጥቃት ቢሠለፉም ህልማቸው እንደጉም በኖ ይቀራል እንጅ ተፈጻሚ አይሆንም ብለዋል፡፡ አቶ ዳኝነት ግብጽ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተፈጻሚ እንዳይሆን ብትወተውትም ኢትዮጵያ ውትወታውን ወደጎን በመተው በወሰደችው ቆራጥ እርምጃ ዳግም አድዋን እያስመዘገበች ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተጠናክሮ ወደ ከፍታ ማደግ ምቾት ያልሠጣቸው ኃያላን ሀገራት አሸባሪው ትህነግን ተጠቅመው ተፅዕኖ ለማሳደር የሚያደርጉት ጥረት ግቡን እንዳይመታ በቅንጅት እና በአንድነት መሥራት ተገቢ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ጀግኖች አባቶች ለዘመናት በደማቸው እና በአጥንታቸው አስከብረዋት የኖረችን ሀገር አሸባሪው ትህነግ ለማፍረስ ባይሳካለትም ተላላኪነቱን ለመወጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው አቶ ዳኝነት የጠቆሙት፡፡ ሊቀመንበሩ እንደተናገሩት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችባቸው አምስት ዓመታት ቅድሚያ የሠጠችው ኢትዮጵያን በዘር፣ በሃይማኖት እና በቋንቋ መከፋፈል ነበር፤ ባይሳካላትም አሸባሪው ትህነግም በስልጣን ዘመኑ ተላላኪነቱን ለመወጣት ተግባራዊ አድርጎታል ብለዋል፡፡ ይህም “ኢትዮጵያ” የሚለውን ሥም ከሰዎች አዕምሮ ለማጥፋት ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንዳልነበር ነው የገለጹት፡፡
የጣሊያኖችን ሌጋሲ ለማስቀጠል የተነሳው አሸባሪው ትህነግ ሥልጣኑን ሲነጠቅ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የትጥቅ ትግል ለማድረግ ግንባር ፈጥሮ እየተዋጋ መሆኑን ሊቀመንበሩ አንስተዋል፡፡ ይኽም በጀግኖች ልጆቿ ተጋድሎ ላይመለስ እንጦሮጦስ የሚገባበት ጊዜ እየመጣ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡
አቶ ዳኝነት እንደገለጹት አሸባሪው ትህነግ እሞትላታለሁ እያለ የሚዋሽባትን ትግራይን ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማሳጣት ሕጻናትን፣ ሴቶችን እና አዛውንቶችን በገፍ ለጦርነት እያሰለፈ ነው፤ ጁንታው ሕጻናትን ለስልጣን ማራዘሚያው እየተጠቀመባቸው ነው፡፡
አሸባሪው ትህነግ ሒሳቤን ከአማራ ሕዝብ አወራርዳለሁ ቢልም መርዙን የተረዳው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ለመመከት እያደረገ ያለው ጥረት ይበል የሚያሠኝ ነው ሲሉ አወድሰዋል፡፡ ዳግም አድዋን ለመዘከር ጊዜው ሩቅ እንደማይሆን በመግለጽ፡፡ አቶ ዳኝነት ኢትዮጵያ የስጋት አደጋ በተደቀነባት ሠዓት ከችግር ለመውጣት ልምድ እንዳላት አንስተዋል፡፡ ጣሊያን ለግፍ ወረራ ስትመጣ፣ ግብጽ ጉንደት እና ጉራ እንዲሁም የሶማሌ ጦርነት ሲታወጅባት በድል እንደመከተቻቸው ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ሌላ ምሳሌ አሉ ሊቀመንበሩ አፄ ምኒልክ ክተት አዋጅ ሲያውጁ በየቀበሌው የጎበዝ አለቃ፣ በወረዳ ምክትል የጦር አለቃ፣ በወረዳ የጦር መሪ፣ በአውራጃ የበላይ የጦር መሪዎችን በመሾም በአንድነት እና በመተባበር ድልን ተቀዳጅተዋል፡፡ አቶ ዳኝነት ጣሊያን ዘመናዊ መሣሪያ ብትታጠቅም ድሉ ለኢትዮጵያ የሆነው በነበረው አንድነትና የሀገር ፍቅር ሥሜት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
እንደ ሊቀመንበሩ ማብራሪያ ኢትዮጵያ ከጠላት ወረራ እንዳትወጣ የሚያደርጓት በርካታ ነገሮች አሉ፤ ድንግል መሬቷ፣ ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ወንዞቿ፣ ተፈጥሮ የቸራት የአየር ንብረቷ የውጭ ጠላቶቿ ዓይናቸውን ከእሷ ላይ እንዳይነቅሉ ምክንያት ናቸው፡፡ በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ግብጽ የአባይን ወንዝ ከመነሻው ለመቆጣጠር ከ13 ሺህ በላይ ወታደሮቿን ብትልክም ወደ ሀገራቸው ሳይመለሱ መቅረታቸውን አቶ ዳኝነት አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንደ ዓይናቸው ብሌን ይጠብቋት ነበር፤ አባቶች ሀገራዊ ችግር ሲያጋጥማቸው ከመከፋፈል ይልቅ አንድነትን፣ ከመለያዬት ይልቅ መተባበርን አጠንክረው ሠርተውበታል፡፡ የአሁኖቹ ወጣቶችም ታሪክን እየደገሙ ነው፤ ይህን የህልውና ዘመቻ ማለፍ የሚቻለው ደግሞ በአንድነት እና በመተባበር ሥሜት በመሠባሠብ ነው ብለዋል፡፡
የማኅበሩ አባላት በተለያዩ መድረኮች የሀገራቸውን ታሪክ ለወጣቱ ለማሳወቅ ጥረት ማድረጋቸውን አቶ ዳኝነት ተናግረዋል፡፡ “የሀገሩን ታሪክ የማያውቅ ወጣት ከብዙ ሴቶች መካከል እናቱን እንደማይለይ ሕጻን ይቆጠራል” ብለዋል፡፡ አቶ ዳኝነት ወጣቱ የሀገሩን ታሪክ ማወቅ፣ መረዳት እና ሀገሩን መውደድ አለበት ብለዋል፡፡ አባቶች የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ በጋራ ይሠሩ እንጂ ከመካከላቸው ባንዳዎች አልጠፉም ነበር፤ የእነዚያ ባንዳዎች ልጆች ናቸው ዛሬም ሉዓላዊነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር ለማፍረስ የመጡት፤ ወጣቱ ይኽን መረዳት አለበት ብለዋል፡፡
ወጣቱ የአባቱን ተጋድሎ መድገም ይጠበቅበታል፤ ለዚህ ደግሞ ሀገሩን መውደድ፣ ታሪኳን ማወቅ እና መረዳት ጊዜ የማይሠጠው ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ አርበኞችም በያሉበት አካባቢ የሀገራቸውን ታሪክ ለልጆቻቸው መንገር፣ ማስረዳት እና ማስገንዘብ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ አቶ ዳኝነት ኅብረተሰቡ መንግሥት ከህልውና ዘመቻው ዝግጅት ጎን ለጎን የአካባቢውን ሰላም በንቃት መጠበቅ አለበትም በማለት አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ