“አሸባሪው የህውሃት ቡድን በትግራይ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ ነው” ትዴፓ

228
“አሸባሪው የህውሃት ቡድን በትግራይ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ ነው” ትዴፓ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በትግራይ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ በመሆኑ በዓለምአቀፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊጠየቅ እንደሚገባ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አስታወቀ።
ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ አሸባሪ ቡድኑ በትግራይ ክልል እያደረሰ ያለውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ በአግባቡ እንዲረዳ ማድረግ ተገቢ መሆኑም ተጠቁሟል።
የትዴፓ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቶ ሙሉብርሃን ሃይሌ፤ አሸባሪው ህወሃት የትግራይን ሕዝብ መሸሸጊያ በማድረግ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለው መሆኑን ገልጸዋል።
ቡድኑ እታገልለታለሁ እያለ ለሚያወራለት ለትግራይ ሕዝብ ምንም ዓይነት ኀላፊነት እንዳማይሰማው ጠቁመው፤ ይህንንም በተደጋጋሚ በፈጸማቸው እኩይ ተግባራት በግልጽ ያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።
ቡድኑ ከስልጣን ከወረደ በኋላ የሚፈጽመው ግፍና በደል ደግሞ እየከፋ መምጣቱን አቶ ሙሉብርሃን ተናግረዋል።
ቡድኑ “ለሕዝብ እታገላለሁ ቢልም ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ ከማድረግ ባለፈ ህጻናትና አቅመ ደካሞችን ጭምር በጦርነት በማሳተፍ ጸረ-ሕዝብነቱን በተግባር እያስመሰከረ ነው” ብለዋል።
ይህም ቡድኑን በዓለምአቀፍ ሕግ በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስጠይቀው መሆኑን ጠቁመዋል።
የፌዴራል መንግሥት ለሕዝቡ በማሰብ የሰጠውን የጥሞና ጊዜ የትግራይ አርሶአደር በአግባቡ እንዳይጠቀም እንቅፋት የሆነው አሸባሪው ህወሓት መሆኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ አሸባሪ ቡድኑ መላ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ህዝቡ እንዲደግፈው የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
“የትግራይ ሕዝብ አሸባሪው ህወሓት በድጋሚ ስልጣን ላይ ይመጣል በሚል በቀቢጸ-ተስፋ ሊጠብቅ አይገባም” ያሉት ኅላፊው፤ ቡድኑ እስኪከስም ድረስ ከሽብር ድርጊቱ እንደማይቆጠብ ተናግረዋል።
መንግሥት የሽብር ቡድኑን እኩይ ተግባር በጥንቃቄ መመከትና የትግራይን ሕዝብ ነጻ ማውጣት እንዳለበትም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያውያን ተጋሩ ሲቪክ ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዮሐንስ ጎይቶም በበኩላቸው፤ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብና ለአርሶአደሩ የእፎይታ ጊዜ ለመስጠት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች በክልሉ ከፍተኛ ስርዓት አልበኝነት እንዲንሰራፋ አድርገዋል።
ለአብነትም ህጻናትና አቅመ ደካማ አረጋውያንን ለጦርነት ከማሰለፍ ጀምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወንጀለኞችን በመልቀቅ ዝርፊያና ህገ-ወጥ ተግባር እንዲበራከት ማድረጉን አንስተዋል።
በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚከሰቱ ግፍና መከራዎች መነሻ አሸባሪው የህወሓት ቡድን መሆኑን ጠቅሰው፤ ቡድኑ ከዓለምአቀፍ የጦር ወንጀለኝነት ባለፈ በዘር ማጥፋት ወንጀል ሊጠየቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የትግራይ ሕዝብም ቡድኑ ለረጅም ዓመታት ሲያደርስበት የነበረውንና አሁንም እያስከፈለው ያለውን ዋጋ በአግባቡ በመረዳት ይህን ኅይል ታግሎ ነጻ መውጣት እንዳለበት አመልክተዋል።
ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የአሸባሪው ህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል እየፈፀመው ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አይቶ እንዳላየ ማለፉ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል።
ቡድኑ በተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ የውጭውን ማኅበረሰብ ለማሳሳት የሚያደርገው ሙከራም በእውነተኛ መረጃ ሊከሽፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አቶ ሙሉብርሃን በበኩላቸው ቡድኑን በእውነተኛ መረጃ ለማጋለጥ ተባብሮ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የአማራ ሕዝብ ሁሉም ፋኖ ነው፣ ሁሉም አርበኛ ነው፣ በዚህ ትግል የማይሳተፍ የአማራ ሕዝብ በፍፁም አይኖርም” አቶ አብርሃም አለኸኝ
Next articleየዛሬ ውሎን የህልውና ዘመቻ አስመልክቶ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ የሰጡት አጭር መረጃ።