
“የአማራ ሕዝብ ሁሉም ፋኖ ነው፣ ሁሉም አርበኛ ነው፣ በዚህ ትግል የማይሳተፍ የአማራ ሕዝብ በፍፁም አይኖርም” አቶ አብርሃም አለኸኝ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 20/2013 ዓ.ም(አሚኮ) የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም አለኸኝ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ባንዳነትን እንደሸማ የተጎናጸፈው አሸባሪው ቡድን ግልፅ የሆነ ጦርነት ከፍቶብናል ብለዋል። መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ቢወስንም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲኦል መግባት ካለብንም እንገባለን በሚል አቅለቢስ ውሳኔ ጦርነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት። የከፈተው የጦርነት ግፍ ኢትዮጵያን ማፈራረስ፣ ሕዝቦቿን ማጎሳቆልና የአማራን ሕዝብ ማጥፋት ነውም ብለዋል።
ጦርነት ካወጀበት ጊዜ ጀምሮ ንጹሐንን ይገድላል፣ የአርሶ አደሩን የጎተራ እህል እና የበሰለ ምግብ ሳይቀር ይዘርፋል ነው ያሉት። የአማራና የአፋርን ሕዝብ እያጎሳቆለ መኾኑንም አንስተዋል።
የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ፣ የሀገር መከላከያና የክልል ኃይሎች በጀግንነት እየተዋጉት ነውም ብለዋል።
አሸባሪው ቡድን ነብሰ ጡርና አካል ጉዳተኞችን ሳይቀር እያዘመተ እየተዋጋ መኾኑንም ተናግረዋል።
በርእሰ መሥተዳደሩ የተጠራውን የክተት ጥሪውን ተቀብለው የአማራ የቁርጥ ቀን ልጆችና የዘመኑ አርበኞች ወደየ ማእከሉ እየገቡ ነው፣ ወጣቶች በከፍተኛ ወኔ እየተነቃነቁ ነው፣ ወጣቶች ለህልውና ዘመቻው ራሳውን እያዘጋጁ ነው፤ ለዚህም ታላቅ አክብሮት አለን ነው ያሉት።
ትግሉ አሸባሪውን ለማጥፋት የሚደረግ ትግል ነው፤ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የመጠበቅና የማዳን ነው፣ አሸባሪው ትህነግ በአፈቃላጤዎቹ አማካኝነት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል እንገባለን ብለውናልም ነው ያሉት።
አሸባሪው ቡድን እድል ካገኘ ኢትዮጵያን ያፈራርሳታል፣ ኢትዮጵያዊያን ያጎሳቁላል፣ በፍፁም እድል ልንሰጠው አይገባም ብለዋል። በግንባር በየአውደ ውጊያው እየተወዳቁ ላሉ ኃይሎች ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የአማራ ሕዝብ ሁሉም ፋኖ ነው፣ ሁሉም አርበኛ ነው፣ በዚህ ትግል የማይሳተፍ የአማራ ሕዝብ በፍፁም አይኖርም።
ቡድኑን ለማጥፋት ሁላችንም አንድ እንሁንም ብለዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራትና መላው የአማራ ሕዝብ በአንድ ግንባር እንሰለፍ፣ የአባቶቻችን ታሪክ ለመድገም በጋራ እንቁም ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
አንድ ስንሆንና ስንተባበር ወያኔ ከፊታችን የመቆም አቅም አይኖረውም ነው ያሉት። ኃይል አልቆበት አርሶ አደርና ሕፃናትን በኃይል እያስከተተ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ሁላችንም ወደ ግንባር እንሂድ፣ ከአሸባሪው ጋር እንፋለም፣ ለዘራፊ ቡድን መበገር የለብንም፣ የኢትዮጵያ መሬት ለአሸባሪው ትህነግ መመቸት የለበትም ነው ያሉት።
መላው የአማራ ሕዝብ አሸባሪው ቡድን በገባበት ሁሉ ሰላም እንዳያገኝ በአባቶቻችን ፍኖት የአባቶቻችን ታሪክ መድገም አለበት ነው ያሉት። አሸናፊዎቹ እኛ እንደምንሆን ጥርጥር የለውምም ብለዋል ኃላፊው።
ጦርነቱ የግፉአን ጦርነት ነው ያሉት አቶ አብርሃም ለእኛ የፍትህ ጦርነት ነው፣ የኢትዮጵያን ሕልውናን ማስከበር ጦርነት ነውም ብለዋል። በዚህ ጦርነት መሳተፍ ጀግንነት እና አርበኝነት ነውም ብለዋል።
ሁሉም አርበኛ መሆን አለበት፤ ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ ሁላችንም ወደ ግንባር መሄድ አለብንም ነው ያሉት።
በአባቶቻችን መንገድ የምንሄድ ለጠላት የማንበገር አሸናፊዎች ነን ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m