
መንግሥት የአሸባሪውን ትህነግ ኋላ ቀር የጦር ስልት አካሄድ ለመቀልበስና የሀገርን ህልውና ለመታደግ ሁሉንም አማራጮች ሊወስድ እንደሚገባ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝባዊ ማዕበል (ሂሁማን ዌይቭ) የጦርነት ስልት በርካታ የሰው ቁጥር በማሰለፍ ጠላትን በቁጥጥር ስር ለማድረግ የሚያገለግል ወታደራዊ ስልት እንደኾነ ይነገራል፡፡ ስልቱ በጠላት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ካለ ፍላጎት በሚደረገው ግብግብ ከፍተኛ የኾነ ሰብዓዊ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ይህ ስልት በቻይና በስፋት ተግባራዊ እንደተደረገም ይነገራል፡፡ የጦርነት ስልቱ ቀደም ሲል ተግባራዊ ቢደረግም የቻይናው መሪ ”ማኦ ዜዶንግ“ በይበልጥ እንደተጠቀመበት በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ቻላቸው ታረቀኝ ገልጸዋል።
መምህር ቻላቸው እንዳሉት ሕዝባዊ ማዕበል ወይንም የባሕር ሞገድ የሚል ትርጓሜ ያለው ይህ የጦርነት ስልት በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝባዊ ማዕበል በማስነሳት በጦርነት ላይ ማሰማራት ነው። በዚህም በቻይናና በኮሪያ ጦርነት ጊዜ ቻይና ተግባራዊ አድርጋው ነበር። በቻይናና በሕንድ፣ በጃፓንና በሩሲያ ጦርነት ጊዜም ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ እአአ ከ1980 እስከ 1988 በኢራን እና ኢራቅ መካከል በተካሄደው ጦርነት ኢራን በድንበር አካባቢ ከፍተኛ ጥፋትን ያስከተለ ሶስት ያልተሳኩ ሕዝባዊ ማእበል ጦርነቶችን ሙከራ አድርጋ እንደነበር ከቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡
በዚህ የጦርነት ስልት የደንብ ልብስ በመልበስ ተመሳስሎ በመግባት ጥቃት በመፈጸም ማደናገር እና መበተን ስልት አድርጎ ሊጠቀም እንደሚችል መምህር ቻላቸው አስረድተዋል።
የውጊያ ስልቱ ትላልቅ የጦር መሳሪያዎች ባልነበሩበት በድሮ ዘመን ቢተገበርም ስልቱ በዚህ ዘመን ዓለም ካፈራችው የጦር መሳሪያዎች ጋር አብሮ የማይሄድ ኋላቀር የጦርነት ስልት እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
ትህነግ በዚህ ዘመን ሊተገበር የማይችል ኋላቀር የጦርነት ስልት በመከተል ሕጻናትን እና ሴቶችን እያስፈጀ መኾኑን ነው መምህር ቻላቸው ያነሱት፡፡ ስልቱ የጦር መሣሪያ አቅርቦት እጥረት በሚያጋጥምበት ጊዜም ተግባራዊ እንደሚደረግ ያነሱት መምህሩ ትህነግም ሕዝቡን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመበት መኾኑን ገልጸዋል።
ትላልቅ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ በዋሉበት በዚህ ዘመን ይህን ስልት ተግባራዊ ማድረግ ትርፉ ኪሳራ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመቀልበስ መንግሥት የተጠና ስልት ሊጠቀም እንደሚገባም መክረዋል፡፡
ባለፈበት የጦርነት ስልት ለትህነግ መጠቀሚያ እየኾነ የሚገኘውን የትግራይ ሕዝብ ማስተማር ተቀዳሚ ተግባር ሊኾን እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
የትህነግን ተግባር ለዓለም ማኅበረሰብ ማሳወቅ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል። ‹‹በተለያየ አጋጣሚ የወታደራዊ የደንብ ልብስ በትህነግ እጅ ሊገባ ስለሚችል የደንብ ልብሱን መፈተሸ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
መንግሥትም የአሸባሪውን ትህነግ ኋላ ቀር የጦር ስልት አካሄድ ለመቀልበስና የሀገርን ህልውና ለመታደግ ሁሉንም አማራጮች ሊወስድ እንደሚገባ መክረዋል።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m