“አሸባሪው ትህነግ የማይካድራውን ጭፍጨፋ እና የ27 ዓመታቱን ጭቆና በየትኛውም ቦታ በማንም ሰው ላይ እንዲደግመው የሚፈቅድ አንድም አማራ የለም” የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች

198

“አሸባሪው ትህነግ የማይካድራውን ጭፍጨፋ እና የ27 ዓመታቱን ጭቆና በየትኛውም ቦታ በማንም ሰው ላይ እንዲደግመው የሚፈቅድ አንድም አማራ የለም” የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ የደቀነውን የህልውና አደጋ ለመከላከል ሁለንተናዊ ዝግጅት ማድረጋቸውን የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት የጠራውን የክተት ጥሪ አስመልክቶ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎችን አነጋግሯል፡፡

አሚኮ ያነጋገረው የደባርቅ ከተማ ነዋሪ እና የወጣቶች አስተባባሪ ወጣት ባንተላይ አየልኝ “የክተት ጥሪው እንደ አማራ ስንጠብቀው የነበረ እና የምንቀበለው ነው” ብሎናል፡፡ ወጣት ባንተላይ የአማራ ሕዝብ የተጋረጠበትን የህልውና አደጋ ቀድሞ ተገንዝቦ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በተባበረ ክንዱ ጠላትን እየመከተና እያጠቃ መቆየቱን አንስቷል፡፡

አስተያየት ሰጪው እንዳለው አሸባሪው ትህነግ የማያዋጣውን ሩጫ ጀምሯል፤ የትግራይን ሕዝብ በጦርነቱ እንዲማገድ እያደረገ ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ግን ለምንና ማንን ጦርነት እንደሚገጥም ቆም ብሎ ሊያስብ ይገባል፡፡


የትግራይ ሕዝብ ይህንን እውነት ሊቀበልና ከእሳት ራሱን ሊያወጣ ይገባል ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡ “ሽብርተኛው ትህነግ ማይካድራ ላይ የፈፀመብንን ጭፍጨፋ አንረሳም፤ ላለፉት 27 ዓመታት የሠራብንን ግፍ ጠንቅቀን እናውቃለን፤ በየትኛውም ቦታ በማንም ሰው ላይ የማይካድራውን ጭፍጨፋ እና የ27 ዓመታቱን ጭቆና እንዲደግመው የሚፈልግ አንድም አማራ የለም” ያሉት ደግሞ አቶ አገርዓለም ሲሣይ ናቸው፡፡ አቶ አገርዓለም “ሽብርተኛው ትህነግ በማይካድራ ወገኖቻችንን የጨፈጨፈ፣ በእሳት ያቃጠለ፣ በገጀራ የቆረጠ፣ ለአሞራ የሰጠ የሰውነት ባህሪ የሌለው አረመኔ ቡድን” ሲሉ ገልጸውታል፡፡

አሁንም ባይሳካለትም በሑመራ ጭፍጨፋውን ሊደግመው ሙከራ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡ አሁን ጦርነት የከፈተው የለመደውን ጭፍጨፋ ለመፈፀም መሆኑን ነው ያነሱት፡፡ አቶ አገርዓለም እንዳሉት ሽብርተኛው ትህነግን ማጥፋት የሁሉም አማራ ብሎም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኀላፊነት ነው፡፡ የደባርቅ ሕዝብ የሽብርተኛው ትህነግን ኃይል ለማስወገድ ከመከላከያ ሠራዊቱ፣ ለልዩ ኃይሉ፣ ከሚሊሻው እና ከፋኖ ጋር መሆኑን አስታውቋል፡፡

ሁሉም ሽብርተኛውን ትህነግ ለመከላከልና ለማስወገድ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ነዋሪዎቹ የክልሉ መንግሥት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ በመቀበል ሽብርተኛው ትህነግን ለመደምሰስ ሁለንተናዊ ዝግጅትና ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አድኖ ማርቆስ – ከደባርቅ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበባሕር ዳር ከተማ የሚኖሩ የቀድሞ የሠራዊት አባላት የተደረገውን የክተት ዘመቻ ለመቀላቀል አሸኛኘት ተደረገላቸው፡፡
Next article“በትግራይ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ችግር ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስደው ሽብርተኛው የትህነግ ቡድን ብቻ ነው” ዶክተር አረጋዊ በርሄ