
በቻይና የአማራ ተማሪዎች ለህልውና ዘመቻው የሚውል ከ72 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአሸባሪው ትህነግ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመመከት የተጀመረውን የህልውና ዘመቻ ለመደገፍ በቻይና የአማራ ተማሪዎች ከ72 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ለተቃጣባት የህልውና ስጋት ምላሽ ከሁሉም ክፍላተ ዓለማት እየመጣ ነው፡፡ ተማሪዎች ከዕለት ጉርሳቸው፣ ህፃናት ከትምህር ቤት ወጪያቸው እና የኢትዮጵያውያን ኮምዩኒቲ ከዕለት ወጪያቸው እየቀነሱ የህልውና ዘመቻውን እየደገፉ ነው፡፡ በሀገረ ቻይና የሚኖሩ ተማሪዎች በኅብረት ተደራጅተው ኢትዮጵያ ድጋፍ ባሻት ወቅት የሚችሉትን ሁሉ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በቻይና ጀጅያን ግዛት ውስጥ የሚኖረው እና የኢትዮጵያ ተማሪዎች ኅብረት ዋና ጸሐፊ ተማሪ ማርዬ በለጠ ከዚህ ቀደም ለአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ድጋፍ የሚውል 154 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሷል፡፡ በተመሳሳይ ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ነግሮናል፡፡
ዛሬም ኢትዮጵያ የህልውና አደጋ እንደተጋረጠባት የተገነዘቡት ተማሪዎቹ ለሕልውና ዘመቻው ድጋፍ የሚውል 72 ሺህ 150 ብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ገቢ ማድረጋቸውን የኅብረቱ ዋና ጸሐፊ ተማሪ ማርዬ በለጠ ለአሚኮ ግልጿል፡፡ ዋና ጸሐፊው እንዳለው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ወደ ቻይና አልመጡም፤ ከዚህ የነበሩትም በርካቶቹ ወደሀገር ቤት ተመልሰዋል፤ ውስን ተማሪዎች (በዊ ቻት) ባደረጉት ዘመቻ ነው ድጋፉ የተሰባሰበው፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ኅብረት በቻይና ቤጂንግ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ተማሪው ነግሮናል፡፡
ኅብረቱ በሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲው ዘርፍ የተሠራው አመርቂ ውጤት በሌሎች ክፍላተ ዓለማት ለሚገኙ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በአርአያነት የሚነሳ ነው ብሎናል፡፡ በርካቶቹ የቻይና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሮፌሰሮች በቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ ውስጥ የሚሠሩ እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ተማሪዎቹ የኢትዮጵያን እውነት ለአስተማሪዎቻቸው በማስረዳት እና ለቻይና መንግሥት ግንዛቤ እንዲፈጥሩ በማድረግ በኩል የተዋጣለት ሥራ ተሠርቷል ነው ያለን፡፡
በቀጣይም የኅብረቱን የሥራ እንቅስቃሴ በማጠናከር በፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ የኢትዮጵያን እውነት ለቻይናውያን በማስረዳት እና በልዩ ልዩ ድጋፎች ዙሪያ በተጠናከረ መልኩ እንደሚሠሩም የኅብረቱ ዋና ጸሐፊ አስረድቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m