“የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን የክተት ጥሪ በመቀበል የህልውና ዘመቻውን ለመቀላቀል ተዘጋጅተናል” የፍኖተ ሰላም ወጣቶች

116

“የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን የክተት ጥሪ በመቀበል የህልውና ዘመቻውን ለመቀላቀል ተዘጋጅተናል” የፍኖተ ሰላም ወጣቶች

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ የፌዴራል መንግሥት ያሳለፈውን የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ከቀበሮ ጉድጓድ ወጥቶ ጠላቴ ነው ብሎ የፈረጀውን የአማራን ሕዝብ መውጋት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ትህነግ የአማራን ሕዝብ ብቻ ሳይኾን ኢትዮጵያ እንድትፈርስ አልሞ እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያውያን አሸባሪው ትህነግን ለመታገል ከዳር እስከዳር ተነስተዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት ሰሞኑን የትህነግን ጥቃት ለመመከትና ሀገሪቱን ከጥፋት ለመታደግ የክተት ዘመቻ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎም ኅብረተሰቡ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ጥሪውን ተቀብለው የህልውና ዘመቻውን ለመቀላቀል ማዕከል የተገኙት የምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ ወጣቶችም ለትግሉ ዝግጅ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወጣት ማተቤ መላኩ አሸባሪውን የትህነግ ቡድንን ለመደምሰስ ከክልሉ መንግሥት ጎን በመቆም የህልውና ዘመቻውን ለመቀላቀል መወሰኑን ነግሮናል፡፡ ትህነግ የአማራን ወጣት በተለያየ መንገድ አንገት እንዲደፋ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል፡፡ ይህ የግፍ አገዛዝ እንዳይመለስ አሸባሪውን ለመደምሰስ በሚደረገው ዘመቻ ለመሳተፍ መወሰኑንም አብራርቷል፡፡

የክተት ጥሪውን ለመቀላቀል ወደ ማእከል ካመሩት ወጣቶች መካከል ሌላኛው ወጣት መንግሥቱ ዓለማየሁ “እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን፤አባቶቻችን የሀገር ፍቅርን በተግባር እያስተማሩ አሳድገውናል፤የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል በህልውናችን ላይ የመጣውን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት ሁሉም በአንድነት ሊቆም ይገባል” ብሏል።

“ወጣቶች የውስጥ ችግሮቻችንን ወደ ጎን በመተው አሁን በህልውናችን ላይ የተጋረጠብንን ጠላታችንን ለመደምሰስ በአንድነት የምንቆምበት ጊዜ ላይ ነን” ያለው ሌላኛው ዘማች ወጣት ፍሬው ስማቸው ነው። አማራ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ሆኖ ይህንን አሸባሪ ቡድን ማጥፋት አለበትም ብሏል::

የገጠመንን የህልውና አደጋ ምክንያት በማድረግ እንዲሁም የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን የክተት ጥሪ በመቀበል ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን የሰላምና ሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች መምሪያ ተወካይ ኀላፊ አለልኝ አሰፋ ተናግረዋል፡፡

አቶ አለልኝ ወጣቱ ስልጠና በመውሰድ የህልውና ዘመቻውን ለመቀላቀል በየቀበሌ ማዕከል በመመዝገብ ላይ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም በዞኑ በ453 ቀበሌዎች ምዝገባ በማካሄድ ወደ ስልጠና መገባቱን አስታውቀዋል፡፡

ወጣቱ በጦር ግንባር መሰለፍ ብቻም ሳይኾን ሰርጎ ገብ እንዳይኖር አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ የሚያስችል ወታደራዊ ስልጠና በየቀበሌ ማዕከላት መሰጠት መጀመሩንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ዘመኑ ይርጋ – ከፍኖተ ሰላም

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleየሀገር መከላከያ ሠራዊቱን የሚቀላቀሉ የአዲስ አበባ ወጣቶች እና የጤና ባለሙያዎች ሽኝት እየተደረገላቸው ነው።
Next articleበቻይና የአማራ ተማሪዎች ለህልውና ዘመቻው የሚውል ከ72 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ፡፡