ኮሚሽኑ አዲሱን የፕሪሚዬር ሊግ “ፎርማት” ውድቅ አደረገ።

117

ባሕር ዳር፡ መስከረም 14/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለ2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የውድድር ዘመን ያቀረበውን “ፎርማት” ውድቅ አድርጓል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፕሪሚዬር ሊጉ 24 ቡድኖች በሁለት ምድብ ተከፍለው እንዲወዳደሩ ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር ይታወሳል።

በመጨረሻም የየምድቦቹ አሸናፊዎች ለዋንጫ እንዲጫወቱ በሚል ነበር ፌዴሬሽኑ “ፎርማቱን” ያቀረበው።

የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አዲስ የሊግ ፎርማቱን በተመለከተ ከክልል እና ከከተማ አስተዳድር ስፖርት ፌዴሬሽኖች ጋር ዛሬ መክሯል። በምክክሩም ፌዴሬሽኑ ያቀረበው አዲስ የሊግ “ፎርማት” ውድቅ እንዲሆን ወስኗል። በበቂ ጥናት ላይ አለመመስረቱ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያራርቅ መሆኑ እና በክለቦች ተቀባይነት አለማግኘቱ ውድቅ ለመደረጉ ምክንያቶች ናቸው።

አማራጭ መፍትሔ ባልቀረበበት ምክክር ክለቦች እና ፌዴሬሽኑ ተመካክረው አዲስ የሊግ አሠራር እንዲያስቀምጡ ነው ኮሚሽኑ ውሳኔ ያሳለፈው።

አዲሱ የውድድር አማራጭ በእግር ኳስ ባለሙያዎች፣ በክለቦች እና በስፖርቱ ቤተሰቦች ተቀባይነት አላገኘም ነበር።

Previous articleበኩር ጋዜጣ መስከረም 12-2012 ዓ.ም
Next articleባርሴሎና በጠባብ ውጤት ቢያሸንፍም ሊዮኔል ሜሲን በጉዳት አጥቷል፡፡