
- “በህልውና ዘመቻው በሙያችን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል” የሁመራ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች
ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በህልውና ዘመቻው በሙያችን ለማገልገል ቆርጠን ተነስተናል ሲሉ በወልቃይት ጠገዴ የሰቲት ሁመራ ዞን የሁመራ አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች ገለጹ።
አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለመደምሰስ እና የሀገርን አንድነት ለማስጠበቅ እየተካሄደ ባለው ዘመቻ የክልሉን ጥሪ ተቀብለው በሙያቸው ለማገልገል በቁርጠኝነት እና በሀገር ፍቅር እንደሚሠሩ የህክምና ባለሙያዎቹ አስታውቀዋል።
በሁመራ አጠቃላይ ሆስፒታል የተኝቶ ህክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር መኩሪያ ግሩም “በግንባር በመገኘት በሙያችን ለማገልገል ዝግጁ ነኝ” ብለዋል።
ዶክተር መኩሪያ ሀገርን ለማዳን መስዋእትነት መክፈል ያለበት ሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የሙያ መስክ የተሰማራው ሠራተኛም ጭምር መሆን አለበት ነው ያሉት።
“እኔም ለሀገሬ ወታደር ነኝ ፤ የሀገሬን ሰላም ለማስጠበቅ እሠራለሁ ” ያሉት ደግሞ ዶክተር ዳኛቸው ሰውዓለም ናቸው።
ዶክተር ዳኛቸው ለሀገሩ መስዋእት ለሚሆን ወታደር ሁሉም የህክምና ባለሙያ በሙያው ሊረዳ ይገባል ነው ያሉት።
በሆስፒታሉ በነርስነት የሚያገለግሉት ህይወት ገብሬ “የጁንታው ርዝራዦች ሀገርን ለማፍረስ እየሞከሩ ነው፤ እኔም በሙያዬ በቁርጠኝነት ለማገልገል እና የሚጠበቅብኝን ኀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
የሆስፒታሉ አስተዳዳሪ ዶክተር በላቸው ፈረደ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል።
የህክምና ባለሙያዎቹ ሁሉም በሚችለው መልኩ ጥሪውን ተቀብሎ በተሰማራበት ሙያ እንዲያገለግል ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ -ከሁመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m