
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሃብት ለማሰባሰብና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ለማሳየት ታላቅ የኢትዮጵያውያን ትዕይንት በዋሽንግተን ዲሲ ተካሄደ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአሜሪካን ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተቋቋመው ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማኅበር አስተባባሪነት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሃብት ለማሰባሰብና ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ለማሳየት ታላቅ የኢትዮጵያውያን ትዕይንት በዋሽንግተን ዲሲ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ዳያስፖራው የጀመረውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራና ለመከላከያ ሠራዊት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ባለፉት አስር ወራት ብቻ በድር ኢትዮጵያ እያከናወነ ያለውን ሃብት የማሰባሰብ ሂደት ሳይጨምር በአሜሪካን ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
በድር ኢትዮጵያም እስካሁን ያሰባሰበው ሃብት ከ785ሺህ ዶላር በላይ መድረሱን አስገንዝበዋል። እየተደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ዳያስፖራው ከድጋፍ ባሻገር በራሱም ኾነ የሌሎችን አቅም በማስተባበር በኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተሳትፎውን እንዲያሳድግ ጠይቀዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢፌዴሪ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በበኩላቸው ዳያስፖራው እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የተጀመረው ትግል አለመጠናቁቅን በመግለጽ ዳያስፖራው ከግድቡም ኾነ ከሌሎች የኢትዮጵያ ጥቅሞች አንጻር የሚያከናውናቸው ተግባራት ፍሬያማ እንዲሆኑ አንድነቱን በማጠናከርና ወዳጆችን በማብዛት እንዲንቀሳቀስ ጠይቀዋል። መረጃው ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m