
አሸባሪዉ ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ የከፈተዉ ጦርነት በሀገር ላይ የተቃጣ ጥቃት በመኾኑ ይህን ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መኾኑን የኦሮሚያ ተመላሽ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ማኅበር ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሕዝቦች ቅንጅታዊ ሥራ ትህነግን ከመንበረ ስልጣኑ እንዳስወገደው ሁሉ አሁንም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጥምረታቸዉን አጠናክረው ከኢትዮጵያ ትከሻ ላይ ላይመለስ እንዲያወርዱት የኦሮሚያ ተመላሽ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ማኅበር ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ገና ከደደቢት በረሃ ሲጠነሰስ ጀምሮ ሀገር የማፍረስ እና ሕዝብን የመከፋፈል ተልእኮን አንግቦ የተነሳዉ አሸባሪዉ የትህነግ ቡድን በስልጣን ዘመኑ ያልነበረን እና ያልተደረገን ትርክት እየፈበረከ አንዱ ሌላዉን በጠላትነት እንዲፈረጅ በማድረግ የኢትዮጵያዊያንን አብሮነት ሲፈታተን ኖሯል ብሏል፡፡
የትህነግ ቡድን ሕዝብን የማቃቃር ተንኮሉ በአማራ እና በኦሮሞ ሕዝቦች ላይ ጎልቶ ይስተዋል ነበር ያለው የኦሮሚያ ተመላሽ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ማኅበሩ ሁለቱ ሕዝቦች ሴራዉን በቀላሉ እንደሚረዱበት በመገንዘቡ እና ለእኩይ ዓላማዉ እንቅፋት እንዳይሆኑበት በማሰብ ነው ብሏል፡፡ ይሁን እንጅ የሁለቱ ሕዝቦች ትስስር በደም ጭምር የተዋሃደ በመሆኑ የማለያየት ሴራዉ ከንቱ ድካም እንደሆነበት ነው የገለጸው፡፡
አሸባሪዉ ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ የከፈተዉ ጦርነት በሀገር ላይ የተቃጣ ጥቃት በመኾኑ ይህን ጥቃት ለመመከት ከአማራ ሕዝብ ጎን እንደሚሰለፍ የኦሮሚያ ተመላሽ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ማኅበሩ ለአሚኮ ገልጿል ፡፡
አሸባሪው ትህነግ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ጠላት እንደሆነ የተናገሩት የማኅበሩ ጸሐፊ መሳይ ታደሰ የማኅበራቸዉ አባላት በመጀመሪያዉ ሕግ የማስከበር ዘመቻ ከመከላከያ ጎን ተሰልፈዉ ግዴታቸዉን እንደተወጡ እና አሁንም አስፈላጊዉን ወታደራዊ ግልጋሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸዉን ነው የተናገሩት፡፡
አሸባሪዉ የትህነግ ቡድን በስልጣን በነበረበት ጊዜ በአማራ እና በኦሮሞ ሕዝቦች ላይ ተነግረዉ የማያልቁ ግፎች እንደፈጸመ ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያን መራር ትግል አድርገዉ ከመንበረ ስልጣኑ እንዳስወገዱት ሁሉ አሁንም በተባበረ ክንድ ሊመክቱት እና ከኢትዮጵያ ትከሻ ላይ ላይመለስ እንዲያወርዱት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያዊነትን በአንክሮ በሚያቀነቅነዉ እና ሀገር የማፍረስ ተግባሩን ከጅምሩ ሲገዳደረዉ በኖረዉ የአማራ ሕዝብ ላይ በህቡዕ ይፈጸምበት የነበረዉ ግፍ አልበቃ ብሎት የጠላትነት ፍረጃዉን በአደባባይ ገልጾ ጦርነት ቢከፍትም የትህነግን መቃብር ለማፍጠን መላ ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከ ዳር ትብብራቸውን ቀጥለዋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ