
“የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ውስጥህን አጥራ፤ ትጥቅህን አጥብቅ፤ መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ እንደ ትናንቱ ታሪክ ሠርታችሁ አኩሩን፤ ታሪክ እንድንሠራም ምሩን” የሃይማኖት አባቶች
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሕዝብ የክልሉ መንግሥት ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ በመቀበል ለህልውናው መዝመት እንዳለበት የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ሕዝብ በትግሉ ነጻ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ ደስታውን እያጣጣመ ነው ብለዋል ትናንት በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሃይማኖት አባቶች።
በአማራና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ትህነግ ያወጀው ሀገር የመጥፋት እኩይ ሴራን በአንድነት ተጋፍጦ መመከት እንደሚገባም ነው የመከሩት።
የአማራ ክልል መንግሥት ለሕዝቡ የክተት አዋጅ ማሰማቱ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎም በተለይ ወታደራዊ ልምድ ያላቸው ሁሉ ጥሪውን ተቀብለው መዝመት እንደሚገባ አንስተዋል። ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ጉዳዩ የእያንዳንዱን ቤት እያንኳኳ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል አሳስበዋል።
የሃይማኖት አባቶቹ እንዳሉት ኢትዮጵያ ፈጣሪዋ ስላለ አትፈርስም፤ እውነትን እና ፈጣሪን ይዞ የታገለ ሁሉ እንደትናንቱ ያሸንፋል። “የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ውስጥህን አጥራ ትጥቅህን አጥብቅ፤ መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ እንደትናንቱ ታሪክ ሠርታችሁ አኩሩን፤ ታሪክ እንድንሠራም ምሩን” ብለዋል።
አንድነትን በማጠናከር እና ውስጥን በማጥራት የተጋረጠውን የሕልውና አደጋ በቀላሉ መቀልበስና አጸፋዊ ርምጃ መውሰድ ይቻላል ብለዋል የሃይማኖት አባቶቹ።
የሃይማኖት አባቶችም በጸሎት ድጋፋችንን እናደርጋለን ብለዋል። በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንም የድርሻቸውን አስተዋዕኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ