
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የአማራንና የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል የቀደመውን ዝግጁነት እንዲያረጋግጥ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ጥሪ አቀረቡ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 18/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሰልፉ ዓላማ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ክብር ለመስጠት፣ ለሁለተኛው ዙር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ደስታን ለመግለጽ፣ አሸባሪውን ትህነግ ማውገዝ እና ሕዝቡ የሕልውና ዘመቻው ተሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ ነው ተብሏል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥንተ ጠላት የሆነው አሸባሪው ትህነግ በሕዝብ ላይ ለዳግም ወረራ ተነስቷል ብለዋል፡፡ ይህን ኀይል ለማጥፋት የክተት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ትህነግ በአማራ ደም ቆምሮ የታላቋን ትግራይ ምስረታ እውን ለማድረግ ባለፉት ዓመታት አማራን ሲገድል፣ ሲያፈናቅል፣ ሀብትና ንብረቱን ሲዘርፍ፣ ማንነቱን ቀምቶ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ዋና አስተዳዳሪው ለዚህ በሕዝብ ትግል አሁን ወደ አማራ ክልል የተጠቃለሉት ወልቃይት ጠገዴ፣ ሰቲት ሑመራ፣ ራያ እና ጠለምት ወረዳዎች ሁነኛ ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
ቡድኑ አሁንም የአማራን ሕዝብ በማጥፋት ሀገር ለማፈራረስ ሠይጣናዊ እቅድ ይዞ ዳግም መነሳቱን አስገንዝበዋል፡፡ ጁንታው አቅማቸው ለውትድርና ያልደረሱ ሕፃናት እንዲሁም አቅመ ደካሞችን ከእረኛ እስከ ምሁር በዘመቻው አሠልፎ አማራን እየወጋ ነው ብለዋል፡፡
ዋና አስተዳደሪው የትህነግ አሸባሪ ቡድን የኢትዮጵያን ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በጠላትነት ፈርጆ የተነሳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጁንታው በጠለምት፣ በራያ እና በአፋር አዋስኝ አካባቢዎች የከፈተው ተኩስ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲነሳ እኛ ደግሞ እንደ ሕዝብ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማዳን አንድ ሆነን መረባረብ አለብን ብለዋል፡፡ በመሆኑም አቅሙ ግንባር ለመሄድ የደረሰ ማንኛውም ወታደራዊ ሕጉን የሚያሟላ ሁሉ የጥንተ ጠላቱን ለመቅበር የክተት አዋጁን መቀበል አለበት ነው ያሉት፡፡
በትግሉ በመንግሥት መዋቅር ሥር ያለው ልዩ ኀይል እና ሚሊሻ ብቻ ሳይሆን ሕዝባዊ ኀይል የሚሠለፍበት ጭምር በመሆኑ ፋኖዎች የዘመቻው ጉልበት ናቸው ብለዋል፡፡ መሠረታዊ እውቀት እና ልምድ ያለው ሁሉ ግንባር ቀደም ተሠላፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መላው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ መንግሥት በሚሠጠው መመሪያ መሰረት ሀገሪቱን ለመታደግ ቆርጦ መነሳት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ወጣቱ ጊዜ ሳያባክን በመከላከያ ሠራዊት እና በአማራ ልዩ ኀይል ታቅፎ መሠረታዊ ሥልጠናዎችን እንዲያገኝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አቶ አሸተ በሁሉም አካባቢ ተጠባባቂ ኃይል ማፍራት የዘመቻው አካል በመሆኑ የዞኑ መንግሥት እንደ አንድ ቁልፍ ተግባር አድርጎ ይሠራል ብለዋል፡፡
ጦርነቱን በገንዘብ እና በአይነት መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የገንዘብ ድጋፉ የክልሉ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ በከፈታቸው የሒሳብ ቁጥሮች መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በዓይነት የሚደደረገው ድጋፍ የሁሉንም ቤት የሚያንኳኳ ስለሆነ ሁሉም እንደየ አቅሙ በግንባር ለተሠለፈው ወገኑ በማድረስ ለወገኑ ያለውን ፍቅር ማሳየት ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡ የተጀመረውን ድጋፍም አበረታች መሆኑን አንስተዋል፡፡
የውትድርና ሕጉ የሚፈቅድለት የአማራ ወጣት በሙሉ ወታደራዊ ስልጠና ለመውሠድ ራሱን ማዘጀጋጀት እንዳለበት አቶ አሸተ ተናግረዋል፡፡ አቅሙ የፈቀደ ሁሉ ሳያመነታ በሀገር ህልውና ላይ የተጋረጠውን ችግር ለመጋፈጥ ግድ ይላል ብለዋል፡፡ ወጣቶች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የውትድርና ሥልጠና እንዲወስዱ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ ነው ያሉት፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የአማራንና የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል የቀደመውን ዝግጁነት እንዲያረጋግጥ አሳስበዋል ዋና አስተዳዳሪው፡፡ አካባቢያቸውን ከሠርጎ ገብ እና ከፀረ ሰላም ኃይሎች እንዲሁም ውስጣቸው ካለ ባንዳ ነቅተው እንዲጠብቁም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የተለዬ እንቅስቃሴ ሲመለከቱ ለሚመለከተው አካል እንዲያሳውቁ ፤ በሕዝቡ መሀል የተሠገሠጉ ለጠላት ዓይን እና ጆሮ ሆነው የሚያገለግሉ ባንዳዎችን ሲመለከቱ ያለምንም ርህራሄ አሳልፈው መስጠት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
አቶ አሸተ በህልውና ትግሉ ለመሳተፍ ምንም አይነት መዘናጋት መኖር የለበትም ብለዋል፡፡ ሁሉም ጠላትን ለመመከት መውጣት አለበት ነው ያሉት፡፡ ትግሉ ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚሹ የውጭ ጠላቶቻችን እጅ እንዳለበት ለማወቅ ተችሏል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ለማንኛውም ኃይል እንደማትንበረከክ ለማሳየት ታሪክ አጭቶናል፤ የእነ ራስ ቢትወደድ፣ የእነ አባ ደፋር፣ የእነ ራስ አሞራው ውብነህ ልጆች መሆናችንንን በማሳየት የኢትዮጵያ አሸባሪ የሆነውን የትህነግ ነቀርሳ ቡድን ነቅለን እንጥላለን ብለዋል፡፡
ለዚህም ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች ከጎናችን ተሰልፈዋል፤ በተባበረ ክንድ በመዝመት ጠላታችን ላይ ድል እንጭናለን ብለዋል አቶ አሸተ፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4